የቱኒዝያ ፕሬዚዳንት አዲስ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሾሙ
ፕሬዚዳንት ካይስ ሴይድ ከሳምንት በፊት የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርና ፓርላማ ከስራ አግደዋል
ፕሬዚዳንቱ ባለስልጣናትን ያገዱት የኮቪድ 19ኝን ስራ በሚገባ አልመሩም በሚል ነው
የቱኒዝያ ፕሬዘዳንት ካይስ ሴይድ አዲስ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር መሾማቸው ተነግሯል።
ፕሬዘዳንት ካይስ ሴይድ ባሳለፍነው እሁድ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣን ማንሳታቸውን ተከትሎ አገሪቱ በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ ገብታለች።
ፕሬዘዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የእንደራሴ ምክር ቤቶችን እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎችን ከስራ አግደዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ፕሬዘዳንት ካይስ ሪዳ ጋርሳሎይን የአገር ውስጥ ሚኒስትር አድርገው መሾማቸውን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን አፍሪካ ዘግቧል።
አዲሱ ተሿሚ በጸረ ሽብር፣ የደህንነት ስራዎች እና ሎጅስቲክስ አስተዳድር ጥሩ ልምድ ያላቸው ሰው ናቸው ተብሏል።
የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ካይስ ሰይድ ከኮቪድ 19 ሳቢያ በሀገሪቱ የተከሰተውን አመጽ ተከትሎ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከኃላፊነት ማንሳታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ በመላው ቱኒዚያ የተከሰተውን አመጽ ተከትሎ በያዝነው ሳመንት የሀገሪቱን ፓርላማ ከስራ ማገዳቸውም አይዘነጋም።
ይሁንና የፕሬዘዳንቱ ውሳኔ በቱኒዝያ የፓርላማ አባላት እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመቃወም ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
የቱኒዝያ ፓርላማ ቃል አቀባይ እንዳሉት የፕሬዘዳንቱ ውሳኔ ህጋዊ ያልሆነ እና መፈንቅለ መንግስት መሆኑን ተናግረዋል።
በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ቱኒዚያውያን የሀገሪቱ መንግስት የኮቪድ 19ን የያዘበት መንገድ አግባብ አይደለም በሚል ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸው ይታወቃል።
የዓረብ ጸደይ አብዮት መነሻየሆነችው ቱኒዚያ የተሳካ የዲሞክራሲ አብዮት የተካሄደባት በሚል ስትነሳ የቆየች ሲሆን አሁን ወደገጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋት ወደከፋ ቀውስ ሊወስዳት ይችላል የሚሉ ስጋቶች በመነሳት ላይ ይገኛል።