ተቃዋሚዎች የሕገ መንግስት ማሻሻያ ሂደት ለፕሬዝዳንቱ ያልተገደበ ስልጣን ይሰጣል እያሉ ነው
የቱኒዚያ ዜጎች ሕገ መንግስት ይሻሻልበታል የተባለውን ህዝበ ውሳኔ እያካሄዱ መሆኑ ተገለጸ።
ፕሬዝደንት ካይስ ሰኢድ ያቀረቡትን አዲስ ሕገ መንግስት ተግባራዊ ለማድረግ ዜጎች ድምጽ እየሰጡ ናቸው። ሕገ መንግስቱ አዲስ አምባገነን ለማዋለድ ያለመ እንደሆነ የሚገልጹ ዜጎች መኖራቸው ተሰምቷል።
ቱኒዚያውያን ይህንን ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ድምጽ እየሰጡ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ብዙ ድምጽ ሰጭዎች ግን አልወጡም ተብሏል።
በርካታ ዜጎች በዚህ ድምጽ አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ ያልተሳተፉት ሀገሪቱን ወደ አምባገነናዊ አገዛዝ ሊወስዳት ይችላል በሚል ፍራቻ እንደሆነ እየተገለጸ ነው።
ብዙዎች ይህንን ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ በመቃወም አድማ እንደሚያደርጉ እየተጠበቀ ነው። አንዳንድ የተቃውሞ አዝማሚያ አድርገዋል የተባሉ ሰዎችም እየታሰሩ እንደሆነ ተገልጿል።
አዲስ ሕገ መንግስት ስራ ላይ የማዋሉ ሂደት የፕሬዝዳንት ካይስ ሃሳብ መሆኑ ለብዙዎች አልተዋጠላቸውም። የሀገሬው ሰዎች ስጋት ስልጣን በአንድ ሰው እጅ ሊወድቅ የሚል እንደሆነ እየተገለጸ ነው። ይሁንና የፕሬዝዳንት ካይስ ደጋፊዎች ይህ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲሆን ፍላጎት አላቸው ተብሏል።
የፕሬዝዳንት ካይስ ደጋፊዎች በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ለምትገኘው ሀገር መፍትሄው የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ስለመሆኑም እርግጠኞች ናቸው ተብሏል።
የፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ይህ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ሂደት ለፕሬዝዳንቱ ያልተገደበ ስልጣን ይሰጣል እያሉ ነው።