ትራምፕ ክሪሚያን የሩሲያ አካል አድርገው እውቅና ለመስጠት እያሰቡ ነው ተባለ
የፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር ወደፊት በሚደረገው ድርድር ሩሲያ በ2014 የጠቀለለቻትን ክሪሚያን የሩሲያ አካል አድርገው እውቅና ለመስጠት እያሰበ ነው ተብሏል

ፕሬዝደንት ትራምፕ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በሚያደርጉት የስልክ ውይይት የሩሲያው ፕሬዝደንት ተኩስ ለማቆም እንዲስማሙ ለማሳመን እንደሚሞክሩ ተገልጿል
ፕሬዝደንት ትራምፕ ክሪሚያን የሩሲያ አካል አድርገው እውቅና ለመስጠት እያሰቡ ነው ተባለ።
የፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ወደፊት በሚደረገው ድርድር ሩሲያ በ2014 የራሷ ግዛት አድርጋ የጠቀለለቻትን የክሪሚያ ግዛት የሩሲያ አካል አድርገው እውቅና ለመስጠት እያሰበ መሆኑን ሮይተርስ የሴማፎር የዜና ድረገጽን ጠቅሶ ዘግቧል።
ሴማፎር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው አሜሪካ ተመድ ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ ልታቀርብ ትችላለች።
ሴማሮር ከኃይትሀውስ መረጃ አለማግኘቱን ጠቅሷል።
ትራምፕ እስካሁን ይፋዊ ውሳኔ አለማሳለፋቸውን የገለጸው ሴማፎር ክሪሚያን የሩሲያ አካል አድርጎ እውቅና የመስጠት ጉዳይ ወደፊት ከሚቀርቡ አማራጮች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሷል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ በዛሬው እለት ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሚያደርጉት የስልክ ውይይት የሩሲያው ፕሬዝደንት ተኩስ ለማቆም እንዲስማሙ እና ሶስት አመታት ያስቆጠረው ጦርነት በዘላቂነት የሚቆምበትን እርምጃ እንዲወስዱ ለማሳመን እንደሚሞክሩ ተገልጿል።
ክሪሚያ በአለምአቀፍ ደረጃ በአብዛኛው ሀገራት የዩክሬን ግዛት አካል እንደሆነች የምትታወቅ ሲሆን ኪቭ ምንምእንኳን አሁን ላይ በኃይል ለማስመለስ የሚቻል ባይሆንም የጥቁር ባህሯን ባህረሰላጤ ማስመለስ ትፈልጋለች።
ክሬሚሊን የሩሲያ የጥቁር ባህር ኃይል ያለባትና ከመጠቃለሏ በፊት በአብዛኛው ሩሲያኛ ተናጋሪዎች የነበሩባት ክሪሚያ በይፋ የሩሲያ አካል መሆኗን በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል።
በ2014 ክሬሚያን የጠቀለለችው ሩሲያ በየካቲት 2022 በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ በመክፈት በምስራቅና ደቡብ ዩክሬን አራት ግዛቶችን በከፋል ይዛለች። ሩሲያ እነዚህን በከፋል የያዘቻቸውን ግዛቶች የሩሲያ አካል ማድረግ በሀገሪቱ ፓርላማ አጸድቃለች።