አሜሪካ ማዕቀብ የሚጥሱ የቱርክ ኩባንያዎች ላይ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች
ቱርክ በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ኬሚካሎች፣ ማይክሮ ችፕ እና ሌሎች ምርቶችን ወደ ሩሲያ እየላከች ነው ስትል አሜሪካ አስታውቃለች ።
ዋሽንግተን ማዕቀብ የሚጥሱ የቱርክ ኩባንያዎችን ወይም ባንኮችን ለመቅጣት እርምጃ እንደምትወስድም አስጠንቅቃለች።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ባለስልጣን ብራየን ኔልሰን የቱርክ መንግስትና የግሉ ዘርፍ መሪዎች ሐሙስና አርብ አነጋግረው፤ የእቃዎችን ፍሰት ለማደናቀፍ የበለጠ ትብብር ጠይቀዋል።
ባለስልጣኑ ለባንክ ሰራተኞች ባደረጉት ንግግር በዓመቱ ወደ ሩሲያ በተላኩ ምርቶች መጨመር ታይቷል ብለዋል።
"የሩሲያ ወታደራዊ ማምረቻ ሊጠቀምባቸው ከሚችሉ ሁለ-ገብ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ግብይቶችን ለማስቀረት ተጨማሪ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል " ብለዋል።
ብራየን ኔልሰንና የልዑካን ቡድናቸው ወደ ሩሲያ የተላኩ በአስር ሚሊዮኖች ዶላር የሚገመት ምርት ነው ያሉ ሲሆን፤ ይህም ስጋቶችን እንዳስነሳ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ "ምንም የሚያስደንቅ ነገር የለም። ሩሲያ በቱርክ ያላትን ታሪካዊ የኢኮኖሚ ትስስር በትጋት እየፈለገች ነው" ብለዋል።
ጥያቄው የቱርክ ምላሽ ምን ሊሆን ነው የሚለው መሆኑንም ጠቅሰዋል። የኔቶ አባል የሆነችው አንካራ በመርህ ደረጃ በሩሲያ ላይ የተጣለውን ከፍተኛ ማዕቀብ ተቃውማለች።
የምዕራባውያን ሀገራት የወጪ ንግድ ቁጥጥሮችን እና ማዕቀቦችን ከአንድ ዓመት በፊት ተግባራዊ አድርገዋል።
ሆኖም የአቅርቦት መስመሮች ከሆንግ ኮንግ፣ ቱርክ እና ሌሎች የንግድ ማዕከሎች ክፍት ሆነው ቀጥለዋል።