የሩሲያ እና የቱርክ ፕሬዝዳንቶች ምጣኔሃብታዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው ይታወሳል
አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ባላት ግንኙነት ቱርክን አስጠነቀቀች፡፡
አንካራ ከድርጊቷ የማትታቀብ ከሆነ ማዕቀብ ሊጠብቃት እንደሚችል ዋሽንግተን አሳስባለች፡፡
ከሩሲያ ጋር የንግድ ግንኙነቶችን ማድረግ የሚቀጥሉ ከሆነ ማዕቀብ ሊጠብቃቸው እንደሚችል የሚያሳስብ ደብዳቤ ከአሜሪካ ግምጃ ቤት እንደደረሳቸው የቱርክ የንግድና ዘርፍ ማህበራት አስታውቀዋል፡፡
አሜሪካ፤ ሩሲያ እና ቱጃሮች በቱርክ የንግድ ሸሪኮቻቸው በኩል ከተጣለባቸው ማዕቀብ ለመሸሽ እንቅስቃሴዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል ሁኔታዎችን በንቃት እየተከታተለች ነው፡፡
የሩሲያ እና የቱርክ ፕሬዝዳንቶች ምጣኔሃብታዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ከወር በፊት በሪዞርት ከተማዋ ሶቺ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡
ቱርክ ከሩሲያ ጋር ያላት የወጪ ንግድ መጠን ካሳለፍነው ግንቦት ወዲህ በእጥፍ እየጨመረ ነው፡፡ ከሩሲያ የምታስገባው የነዳጅ መጠንም ጨምሯል፡፡ ነዳጁን በሩብል ለመግዛትም በቅርቡ ተስማምታለች፡፡
ይህን ተከትሎ ባሳለፍነው ግንቦት ወደ አንካራ ጎራ ያሉት የአሜሪካ ግምጃቤት ምክትል ገዢ ስለ ሁኔታው አስጠንቅቀው ነበር፤ በማዕቀብ ስር ካሉ የሩሲያ ተቋማት ጋር ግንኙነት ማድረግ ለማዕቀqብ እንደሚዳርግ በማሳሰብ፡፡
ሆኖም፤ ምንም እንኳን የኔቶ አባል ብትሆንም ልክ እንደሌሎች ምዕራባውያን ሁሉ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያልፈለገችው ቱርክ ከሩሲያም ሆነ ዩክሬን ጋር ገለልተኛ መስላ መታየትን መርጣለች፡፡
ይህም በሩሲያ ነዳጅ ላይ ካላት ጥገኝነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ተናግረዋል፡፡