በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ቱርክን ለ20 ዓመታት የመሩተ ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቃቸዋል
የቱርክ ፕሬዝዳንታዊ እና የፓርላማ አባላት ምርጫ በበዛሬው እለት እለት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በርካታ ቱርካውያን ለቀጣይ 5 ዓመታት ሀገራቸውን የሚመራ ፕሬዝዳንት እና የፓርላማ ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ በማለዳ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በማቅናት ድምጽ እየሰጡ ይገኛሉ።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ሬስፕ ጣይብ ኤርዶሃን እና የስድስት ፓርቲዎችን ድጋፍ ያገኙት ከማል ክሊችዳሮግሉ ይፎካከራሉ።
24 ፓርቲዎችና 151 የግል እጩ ተፎካካሪዎች 600 መቀመጫ ባለው የቱርክ ፓርላማ ወንበር ለማግኘት የመራጮችን ድምጽ ይጠባበቃሉ።
የዋጋ ግሽበት እና በየካቲት ወር የደረሱት የርዕደ መሬት አደጋዎች በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት የኤርዶሃን ተቃዋሚዎች በስፋት አንስተዋቸዋል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት የሀገሪቱን የኑሮ ውድነት ወደ ነጠላአሃዝ እንደሚያወርዱ ቃል የገቡ ሲሆን፤ የመንግስት ሰራተኞችን ደመወዝም በ45 በመቶ ጭማሪ አድርገውበታል።
የፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ተቀናቃኝ የቱርክ ሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ መሪው ክሊችዳሮግሉ ኤርዶሃን በ2018 ዳግም ሲመረጡ የቀየሩትን የፕሬዝዳንታዊ ስርአት ወደነበረበት ፓርላሜንታዊ ስርአት እመልሰዋለሁ ብለዋል።
64 ሚሊየን ቱርካውያን በምርጫው መሳተፍ እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፥ ከ2 ሚሊየን በላይ ከቱርክ ውጭ የሚገኙ የሀገሪቱ ዜጎችም በያሉበት ድምጻቸውን ሲሰጡ መሰንበታቸውን ቲአርቲ አስነብቧል።