የቱርክ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ ሊካሄድ እንደሚችል ተነገረ
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን በትናንቱ ምርጫ መምራት ቢችሉም 50 ከመቶና ከዚያ በላይ ድምጽ አላገኙም
ተፎካካሪያቸው ከማል ክሊችዳሮግሉ 44 ነጥብ 97 ድምጽ ማግኘታቸው ተገልጿል
ቱርክ በትናንትናው እለት ፕሬዝዳንታዊ እና የፓርላማ አባላት ምርጫ አካሂዳለች።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው 55 ነጥብ 3 ሚሊየን መራጮች ድምጽ የሰጡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን 49 ነጥብ 39 መራጭ ማግኘታቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ምክር ቤት አስታውቋል።
ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ከማል ክሊችዳሮግሉ ደግሞ 44 ነጥብ 97 ድምጽ ማግኘታቸውን ነው ቲአርቲ ያስነበበው።
ሲጋን ኦጋን የተሰኙት የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ተፎካካሪም 5 ነጥብ 20 በመቶ መራጭ እንዳገኙ በቆጠራው ተረጋግጧል።
የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው የድምጽ ቆጠራ 99 ነጥብ 20 ከመቶ ቢጠናቀቅም አሸናፊውን የሚለይ አልሆነም።
በቱርክ የምርጫ ህግ ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት እጩ ሆኖ የቀረበው አካል 50 ከመቶ እና ከዚያ በላይ መራጭ ማግኘት እንዳለበት ተጠቅሷል።
በዚህም መሰረት 50 ከመቶ መራጭ ያገኘ አካል ባለመኖሩ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው በድጋሚ እንደሚካሄድ ነው እየተዘገበ ያለው።
የዳግም ምርጫ ፉክክሩ ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚደረግ ሬውተርስ ዘግቧል።
ቱርክን ለሁለት አስርት የመሩት ኤርዶሃን በድህረ ምርጫው ከተሰጣቸው ይሁንታ በበለጠ በምርጫው ከፍተኛ ድምጽ ማግኘታቸውን የሚጠቅሰው ዘገባው፥ በዳግም ምርጫውም የተሻለ ድምጽ ሊያገኙ እንደሚችሉ አመላክቷል።
የናሽናሊስት ሞቭመንት ፓርቲው ሲጋን ኦጋን (5 ነጥብ 2 በመቶ መራጭ ያገኙ) ለኤርዶሃን ወይንስ ለክሊችዳሮግሉ ድጋፍ ይሰጣሉ የሚለውም ተጠባቂ ነው።
በድጋሚ የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን ውጤት ከክሬምሊን እስከ ዋይትሃውስ በጥብቅ ይከታተሉታል።