ቱርክ የቴሌቪዥን ዜና አንባቢዋን ከስራ አገደች
ዜና አንባቢዋ የታገደችው ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አለው የተባለው የስታር ባክስ ቡናን ይዛ በመቅረቧ ነው
ቱርክ ስታር ባክስን ጨምሮ የእስራኤል ጦርን ይደግፋሉ በሚል ማገዷ ይታወሳል
ቱርክ የቴሌቪዥን ዜና አንባቢዋን ከስራ አገደች፡፡
የቱርኩ ቲጂአርቲ የተሰኘው መንግስታዊ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሜልተም ጉናይ የተሰኘችውን አንጋፋ ዜና አንባቢ ከስራ ማገዱ ተገልጿል፡፡
ጋዜጠኛዋ በዜና ሰዓት የአሜሪካው ስታርባክስ ቡናን ይዛ መቅረቧ ብዙዎችን ያስቆጣ ሲሆን የሚዲያው አመራሮችም ጋዜጠኛዋ ህግ በመጣስ ላደረገችው ድርጊት ከስራ ማገዳቸውን አስታውቀዋል፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያው በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ ጋዜጠኛ ሜልተም የድርጅቱን ህጎች በመጣስ በቀጥታ ስርጭት ወቅት ብዙ ስህተቶችን እንደፈጸመች ገልጿል፡፡
ቱርክ እስራኤልን ይደግፋሉ በሚል ኮካ ኮላ እና ኔስትል ምርቶችን አገደች
ስታርባክስ ኩባንያ ከእስራኤል-ጋዛ ጦርነት በተጨማሪም በቀጥታ ስርጭት ወቅት የትኛውንም ምርት ማስተዋወቅ እንደማይቻል የሚደነግገው የድርጅቱ ህግ መጣሱንም አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ከጋዜጠኛ ሜልተም በተጨማሪ የቴሌቪዥኑ ዳይሬክተርም ከስራ የታገደ ሲሆን የቴሌቪዥኑ ድርጊት የብዙ ብዙሃን መገናኛዎችን ትኩረት ስቧል፡፡
ቱርካዊያን በጋዛ እየተፈጸመ ያለው ሰቆቃን በስፋት እየተቃወሙ ካሉ ህዝቦች መካከል ዋነኞቹ ሲሆኑ ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ስህተቶችን እንደማይታገሱ ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያው ሁሌም ቢሆን ከፍልስጤማዊን ጎን እንደሚቆም የገለጸ ሲሆን ላስቀመጣቸው ህጎችም ተገዢ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡
ዓለም አቀፉ የቡና ሻጭ ኩባንያ ስታር ባክስ ከእስራኤል ጎን እንደሚቆም መግለጹን ተከትሎ በተለያዩ ሀገራት ምርቱ እየታገደበት ይገኛል፡፡
የድርጅቱ ሰራተኞች ማህበር ስታርባክስ ኩባንያ ጦርነቱን ለገበያው ለመጠቀም እየሞከረ መሆኑን የኮነነ ሲሆን ኩባንያው በበኩሉ በማንኛውም አካል ላይ የሚፈጸም ሽብርተኝነትን እና ጥላቻን እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡