ኢትዮጵያ ቱርክ እና ሶማሊያ የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት እንቅልፍ እንደማይነሳት ገለጸች
ቱርክ እና ሶማሊያ ከሰሞኑ የጋራ ወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል
በዚህ ስምምነት መሰረት ቱርክ ለቀጣዮቹ 10 ዓመታት የሶማሊያን ባህር ለመጠበቅ ተስማምታለች
ኢትዮጵያ ቱርክ እና ሶማሊያ የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት እንቅልፍ እንደማይነሳት ገለጸች።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህ መግለጫ ላይ ከተነሳላቸው ጥያቄ መካከል ሶማሊያ ከቱርክ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማለች። ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የመግባቢያ ስምምነት ሊጎዳ አይችልም? የሚለው አንደኛው ጥያቄ ነበር።
ቃል አቀባዩ በምላሻቸውም " ሶማሊያም ሆነች ቱርክ ሉዓላዊ ሀገር ናቸው፣ የፈለጉትን ስምምነት ከየትኛውም ሀገር ጋር የማድረግ መብት አላቸው። ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት አላት፣ ይህ ወታደራዊ ስምምነት እኛን እንቅልፍ አይነሳንም" ሲሉ ተናግረዋል።
የሶማሊያ ፓርላማ ከቱርክ ጋር የተደረሰውን የወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ስምምነት በትናንትናው እለት አጽድቋል።
ከ14 ቀናት በፊት የሁለቱ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በአንካራ የፈረሙትና በትናንትናው እለት የጸደቀው ስምምነት ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ አልተደረገም።
የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ግን ለ10 አመት ይቆያል በተባለው ስምምነት ቱርክ ለሶማሊያ ባህር ሃይል ስልጠና እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
ሞቃዲሾ በግዛቷ የባህር ክልል ውስጥ ሽብርተኝነት፣ የባህር ላይ ውንብድና እና “የውጭ ጣልቃገብነትን” ለመከላከልም አንካራ ድጋፍ ታደርጋለች መባሉን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ ከቱርክ ጋር የተደረሰው የወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ስምምነት “ሶማሊያ በአለማቀፍ መድረክ ሀቀኛ አጋር” እንዳላት ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ “ ቀኑ ለሶማሊያ ታሪካዊ ቀን” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በበኩላቸው ስምምነቱ በቀጠናው ለሚገኙ ሀገራት ስጋት የሚፈጥር እንዳልሆነ በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል።
ሽብርተኝነት፣ የውጭ ሃይሎች ስጋቶችን እና የባህር ላይ ውንብድናን በጋራ ለመከላከል የተደረሰው ስምምነት ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋርግንኙነትን የሚያሻክርና ጸብ የሚያጭር እንዳልሆነም ነው ያነሱት።
“የቱርክ ወንድሞቻችን በስምምነቱ መሰረት ባህሮቻችን ለ10 አመታት ይጠብቃሉ፤ ከ10 አመት ትብብራችን በኋላ ጠንካራ ባህር ሃይል ይኖረናል” ሲሉም ተደምጠዋል።
ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በበኩሏ ከሁለት ወር በፊት ኢትዮጵያ ጋር ያደረገችው ስምምነት መተግበሩ አይቀሬ መሆኑን አስታውቃለች።