የግብጽ እና ቱርክ መሪዎች ከአስርት አመታት ውጥረት በኋላ በዓለም ዋንጫ ተጨባበጡ
የመሪዎቹ መጨባበጥ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሰፈነው ውጥተር መቀዝቀዙ የሚያመላክት ነው ተብሏል
ግብጽ፤ ቱርክ የሙስሊም ወንድማማቾችን ትደግፋለች በሚል አንካራን ትከሳለች
ለአስርት አመታት ያህል ከቆየው ውጥረት በኋላ የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ ከቱርክ አቻቸው ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር በኳታሩ የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ተጨባብጠዋል፡፡
የመሪዎቹ መጨባበጥ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሰፈነው ውጥተር መቀዝቀዙ የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡
ሮይተርስ ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች እሁድ እለት ሰላምታ ሲሰጡ የሚያሳይ ፎቶ አጋርቷል።
በ2013 የግብጽ ጦር አዛዥ በነበሩት የአሁኑ ፕሬዝዳንት ሲሲ በተመራውና የወቅቱ የግብጽ ፕሬዝዳንት መሀመድ ሙርሲን በጸረ-መንግስት የጎዳና ላይ ተቃውሞዎች ከስልጣን ለማስወገድ በተደረገውና መፈንቅለ መንግስት ወቅት፤ ቱርክ ለሙስሊም ወንድማማቾች ስታደርግ በነበረው ድጋፍ በሁለቱም የቀጠናው ኃያላን መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ምክንያት ሆኗል፡፡
በተጨማሪም ቱርክ በሊቢያ በመንግስት ላይ የምታሳድረው ተጽእኖ ውጥረቱ ይብልጥ እንዲባባስ አድርጎታል፡፡
ይሁን እንጅ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ሁለቱ ሀገራት በቀጠናው ያለውን ልዩነት ለመቅረፍ ባደረጉት ሰፊ ግፊት ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡
በተለይም ቱርክ ከግብጽ፣ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ከእስራኤል እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያለውን ውጥረት ለማርገብ ባደረገችው ጥረት ሁለቱ ሀገራት ባለፈው አመት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል ምክክር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ምንም እንኳን ኤርዶጋን በሀምሌ ወር ከፍተኛ ደረጃ ያለው ድርድር የማይካሄድበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ቢናገሩም የግብጽ ባለስልጣናት ለማንኛውም መቀራረብ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ሲደመጡ ቆይተዋል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ባለፈው ወር መገባደጃ ላይ እንደተናገሩት ቱርክ “በሊቢያ የምትጫወተው ሚና አስካለወጠች” እንደገና የተጀመሩ መደበኛ ንግግሮች እንደሌሉና ሂደቶቹ በሰከነ አኳሃን ማጤን እንደሚያስፈልግ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡