ቱርክ 54 አይነት ምርቶች ወደ እስራኤል እንዳይላኩ አገደች
እገዳው እስራኤል በጋዛ ተኩስ እስክታቆምና የሰብአዊ ድጋፍ ሳይቆራረጥ እንዲገባ እስክትፈቅድ ድረስ ይቆያል ተብሏል
እስራኤል ለቱርክ “ተናጥላዊ” ውሳኔ አጻፋውን እንደምትመልስ ገልጻለች
ቱርክ 54 አይነት ምርቶች ወደ እስራኤል እንዳይላኩ አገደች።
የሀገሪቱ ንግድ ሚኒስቴር ብረት፣ እምነበረድ፣ ሲሚንቶ፣ አልሙኒየም፣ ማዳበሪያ፣ የአውሮፕላን ነዳጅን ጨምሮ በርካታ ምርቶች ወደ ቴል አቪቭ እንዳይላኩ መወሰኑን ገልጿል።
ክልከላው እስራኤል በጋዛ ለአለማቀፍ ህግ ተገዢ ሆና ተኩስ እስክታቆምና ሰብአዊ ድጋፎች ያለምንም ተጽዕኖ እንዲገቡ እስክትፈቅድ ድረስ ይቆያልም ነው ያለው።
እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች አንስቶ ኔታንያሁን በቃላት ሲወርፉ የቆዩት ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን እስራኤል በዘር ጭፍጨፋ የቀረበባትን ክስ እንደሚደግፉ መግለጻቸው ይታወሳል።
ሃማስን “አሸባሪ ሳይሆን ነጻ አውጪ ነው” የምትለው አንካራ፥ ወደ ጋዛ ሰብአዊ ድጋፎችን ስትልክ ቆይታለች።
ኤርዶሃን የጋዛውን ጦርነት ደጋግመው እንደመቃወማቸው ከእስራኤል ጋር የንግድ ግንኙነታቸውን ሳያቋርጡ መዝለቃቸው በቱርካውያን ዘንድ ቅሬታ ሲያስነሳ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ፕሬዝዳንቱ በጋዛ ጉዳይ ጠንከር ያለ አቋም እንዲይዙ የሚጠይቁ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን፥ በቅርቡ በተደረገው የአካባቢ ምርጫም የኤርዶሃን ፓርቲ ውጤት እንዲርቀው ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ከእስራኤል ጋር የቀጠለው የንግድ ግንኙነት አንዱ ተደርጎ ተጠቅሷል።
የዛሬው ውሳኔም ቱርክ በጋዛ ከአውሮፕላን ላይ ሰብአዊ ድጋፍ ለመወርወር ያቀረበችው ጥያቄ በእስራኤል ውድቅ መደረጉን ተከትሎ የተላለፈ መሆኑ ነው የተገለጸው።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቱርክ የሀገራቱን የንግድ ግንኙነት የሚያሻክር “የተናጠል” ውሳኔ ማሳለፏ ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል።
ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ “ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ሃማስን ለመደገፍ የቱርክ ህዝብን ጥቅም አደጋ ላይ ጥለዋል፤ እኛም አጻፋውን እንመልሳለን” ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የቱርክ ላኪዎች ማህበር መረጃ እንደሚያሳየው የቱርክና እስራኤል የንግድ ልውውጥ ከጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት በኋላ መቀዛቀዝ ቢያሳይም አንካራ ወደ ቴል አቪቭ የምትልከው ምርት በየወሩ እየጨመረ ነው።
ቱርክ በ2024 የመጀመሪያ ሩብ አመት ወደ እስራኤል 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ብትክም ከባለፈው አመት የ21 ነጥብ 6 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ማህበሩ ጠቅሷል።
የጋዛው ጦርነት እንደተጀመረ ከቴል አቪቭ አምባሳደሯን ያስወታችው ቱርክ ለእስራኤል ለወታደራዊ ግልጋሎት የሚውሉ እቃዎችን መላክ ማቆሟን ማሳወቋ አይዘነጋም።