ሙሽሪት 3 ኪሎግራም ወርቅ ጥሎሽ ያገኘችበት አነጋጋሪው የቱርክ ሰርግ
የባለጠጋ እና ታዋቂ ፖለቲከኛ ልጆች በተጣመሩበት ጋብቻ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ታድመዋል ተብሏል
ከኢራን፣ ሩሲያ፣ ኢራቅና ሌሎች ሀገራት የተጋበዙ እድምተኞችም ቅንጡው ሰርግ ላይ መገኘታቸው ተገልጿል
የቱርኳ ቫን ግዛት ከሰሞኑ ደማቅና ታይቶ የማይታወቅ ሰርግ አስተናግዳለች።
የአካባቢው ተወላጅና ባለጠጋው ሙራት ኢራዝ የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸውን ሞቅ ባለ ድግስ ድረዋል።
ሙሽሪት አስሊ ጉንጉራልፕም በግዛቷ የሚንቀሳቀሰው የናሽናሊስት ሞቭመንት ፓርቲ መሪ ልጅ መሆኗ በአካባቢው አጃኢብ ያስባለ ድግስ እንዲሰናዳ ማድረጉን ነው ዛማን የተባለው የቱርክ ጋዜጣ ያስነበበው።
አዲስ ጎጆ ወጪዎቹ ከወዳጅ ዘመዶቻቸውና ከሰርጉ ታዳሚዎች የተበረከተላቸው ስጦታም በቱርክ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ ሆኗል።
ሙሽሪት 3 ኪሎግራም የሚመዝን የወርቅ ስጦታ አግኝታለች፤ ሂሳቡን ለናንተው እንተወው!
ሙሽራው ባይራም ራዝ ደግሞ ትዳሩ የተቃና ይሆን ዘንድ 4 ሚሊየን የቱርክ ሊራ ተሰጥቶታል።
ለጥንዶቹ የተበረከተው ስጦታ ብቻ ሳይሆን የሰርጋቸው ታዳሚዎች ቁጥርም በቫን ግዛት ከፍተኛው ሆኖ የሚመዘገብ ይመስላል።
ከቢዝነሱም ከፖለቲካውም ዘርፍ የተጋበዙ ከ4 ሺህ በላይ እድምተኞች ውዱ ሰርግ ላይ ታድመዋል።
ከቱርክ የተለያዩ ግዛቶች ባሻገርም ከጎረቤት ኢራን፣ ከኢራቅ፣ ሩሲያ እና አዘርባጃን የተጋበዙ ሰዎችም በሰርጉ ላይ መታደማቸው ተዘግቧል።
የሙሽራው አባት ሙራድ ኢራዝ “ከ4 ሺህ በላይ የምትሆኑ ከቱርክና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ሰርጋችንን ለማድመቅ እዚህ ድረስ ስለተገኛችሁ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ” የሚል ንግግር አድርገዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ መሪው የሙሽሪት አባት ግን ንግግራቸው ወደ ቅስቀሳ አድልቶ ይሁን በሌላ ምክንያት ምን እንደተሰማቸው ያሉት ነገር በዘገባው አልተጠቀሰም።