ሶማሊያ በኢትዮጵያ ጉዳይ የወሰደቻቸውን እርምጃ ዝርዝር ይፋ አደረገች
በሀርጌሳና ጋሮዌ ያሉ የኢትዮጵያ ቆንስላዎች እንዲዘጉና ዲፕሎማቶች በሳምንት ውስጥ ከሀገሪቱ እንዲወጡ አዛለች
በሞቃዲሾ የኢትዮጵያ አምባሳደርም ከሀገራቸው መንግስት ጋር እንዲመክሩ በሚል ከሀገር እንዲወጡ ወስናለች
ሶማሊያ በኢትዮጵያ ጉዳይ የወሰደቻቸውን እርምጃ ዝርዝር ይፋ አደረገች።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከአራት ወራት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣንና እና ተቃውሞን ማስከተሉም አይዘነጋም።
ይህንን ተከትሎም ሶማሊያ የተለያዩ ዲፕሎማያዊ እርምጃዎችን ስትወስድ የቆየች ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ የወሰደቻቸውን እርምጃዎች የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ይፋ አድርጓል።
አዲስ በወጣው የሶማሊያ መንግስት ማብራሪያ መሰረት ኢትዮጵያ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ገብታለች የሚል ነው።
በዚህ መሰረትም በራስ ገዞቹ ሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ ዋና ከተማ በሆኑት ሀርጌሳ እና ጋሮዌ ያሉ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲዘጉ ውሳኔ አሳልፋለች።
በእነዚህ የቆስንላ ጽህፈት ቤቶች የሚሰሩ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እና ሰራተኞች በአንድ ሳምንት ውስጥ ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ መወሰኑ ተገልጿል።
እንዲሁም በሞቃዲሾ የኢትዮጵያ አምባሳደር ወደን አዲስ አበባ ሄደው ከመንግስታቸው ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እንዲመክሩ በመወሰን ከሀገር ማስወጣቱንም አስታውቋል።
የሶማሊያ መንግሥት ላወጣው ውሳኔ መነሻ የሆነው ከሶማሊላንድ ጋር ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ባደረገችው የወደብ ስምምነት ምክንያት ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ያላወጣ ሲሆን አል ዐይን አማርኛ በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
በተያያዘ ዜና የፑንትላንድ ገንዘብ ሚንስትር መሀመድ ፋራህ የመሩት ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ ፑንትላንድ በገንዘብ ሚንስትሯ መሀመድ ፋራህ የተመራው ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉን እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ምስጋኑ አርጋ ጋር መምከራቸውን ተናግረዋል።
የፑንትላንድ ባልልጣናት የአዲስ አበባ ጉብኝት ከሰሞኑ ወቅታዊ ጉዳይ ጋር የማይገናኝ እንደሆነ እና የጉብኝት ፕሮግራሙም የቆየ ቀጠሮ ነው ሲሉ በዛሬው ሳምንታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ባደረጉት የወደብ መግባቢያ ስምምነት ምክንያት የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት እንዲሻክር ምክንያት ሆኗል።
ስምምነቱን ተከትሎም የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኙትን የሀገሪቱን አምባሳደር አብዱላሂ መሀመድ ወርፋን ለምክክር ወደ ሞቃዲሾ መጥራቱን ይታወሳል።