የቱርኩ ፕሬዝዳንት ለይፋዊ ጉብኝት ኤምሬትስ ገብተዋል
ኤርዶሃን ከኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ቢን ዛይድ ጋር ይመክራሉ
ቱርክ እና ኤምሬትስ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትስስር በመፍጠር ላይ ይገኛሉ
ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኋላ በባህረ ሰላጤው ሀገራት የመጀመሪያ ጉብኝታቸው እያደረጉ የሚገኙት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አቡዳቢ ገብተዋል።
ኤርዶሃን የሳኡዲ አረቢያ እና ኳታር ጉብኝታቸውን አጠናቀው ነው አረብ ኤምሬትስ የገቡት።
የፕሬዝዳንት ኤርዶሃን አማካሪ እና የኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ሙቻሂት አርሳላን ከአል ዐይን ተርኪሽ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ቱርክ እና አረብ ኤምሬትስ ከቅርብ አመታት ወዲህ የሁለትዮሽ ትብብራቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ሀገራቱ ከኢኮኖሚ ትብብራቸው ባሻገር ፖለቲካዊ መግባባታቸው እያደገ መሄዱንም ነው ያነሱት።
አቡዳቢ እና አንካራ በቀጠናዊ ጉዳዮች እያደረጉት ያለው ትብብርም “አስደሳች” ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ጂኦፖለቲካ በመረዳትና ልዩነቶች በንግግር እንዲፈቱ በማድረግ ረገድ ባለፉት አመታት ትብብራቸውን ስለማጠናከራቸውም ነው የኤርዶሃን አማካሪ ያብራሩት።
የሶሪያን የእርስ በርስ ጦርነትን ጨምሮ በቀጠናው የሚታዩ ፈታኝ ችግሮችን እንደ ኤምሬትስ ካሉ የቀጠናው ሀገራት ጋር ተቀራርቦ በመነጋገር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም በማከል።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በአቡዳቢ ከኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ቢን ዛይድ ጋር ሲመክሩም የሀገራቱን የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ትብብር በሚያሳድጉ ዘርፎች ላይ ይወያያሉ ነው ያሉት።
ለራሷም ሆነ ለውጭ ሀገር ዜጎች መኖሪያነት ምቹ ከሆነችው ኤምሬትስ ብዙ ልምድ እንቀስማለን ያሉት ሙቻሂት አርሳላን፥ አቡዳቢ ደህንነታቸው የተጠበቀና ዘመናዊ ከተሞችን በመገንባትም ለአለም አርአያ የሚሆን ስራ መከወኗን አብራርተዋል።
ኤምሬትስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ በከወነችው ስራ የ2023ቱን የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ28) ለማስተናገድ በመመረጧም ደስታቸውን ገልጸዋል።