ኤርዶጋን የቱርክ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈጸሙ
ባለፈው ሳምንት ዳግም የተመረጡት ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን "ገለልተኛ" በመሆን እንደሚያገለግሉ ቃል ገቡ
ፓርላማ በተካሄደው ስነ-ስርዓት አንዳንድ የተቃዋሚ ህግ አውጭዎች ከመቀመጫቸው ለመነሳት ፈቃደኛ አልነበሩም ተብሏል
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የሁለት አስርት ዓመታት የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ታሪካዊ በሆነው ሁለተኛ ዙር ምርጫ አሸንፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ "ገለልተኛ" በመሆን እንደሚያገለግሉ ቃል በመግባት ዛሬ ቅዳሜ ለሶስተኛ ጊዜ የፕሬዝዳንትነት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
በኢኮኖሚ ቀውስና ከ50 ሽህ በላይ ሰዎችን በቀጠፈው የየካቲቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ህዝባዊ ቁጣ ቢገጥማቸውም ጠንካራውን የተቃዋሚ ትብብር ማሸነፋቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
ኤርዶጋን 52 ነጥብ 18 በመቶ ድምጽ ሲያሸንፉ፤ ተፎካካሪያቸው ከማል ኪሊዳሮግሉ 47ነጥብ 82 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን ይፋዊ የምርጫ ውጤት ያሳያል።
ኤርዶጋን "እንደ ፕሬዝደንትነቴ በክብሬ በታላቋ የቱርክ ህዝብ ፊት...የሀገሪቱን ህልውና እና ነጻነት ለመጠበቅ በሙሉ ኃይሌ ለመስራት...ያለ አድልኦ ግዴታዬን ለመወጣት ቃል እገባለሁ" ብለዋል።
ኤርዶጋን ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ በፓርላማ ከደጋፊዎቻቸው የአንድ ደቂቃ ጭብጨባ ተደርጎላቸዋል።
አንዳንድ ተቃዋሚ የህግ አውጭዎች ግን ለመነሳት ፈቃደኛ አልሆኑም ተብሏል።
ኤርዶጋን በቃለ መሃላቸው ከ100 ዓመታት በፊት በሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ከተመሰረተው የሪፐብሊኩ ህግ እና መርሆች ላለመውጣት ቃል ገብተዋል።
በፓርላማ በነበረው ስነ-ስርዓት በኋላ በደርዘን የሚቆጠሩ የዓለም መሪዎች በመዲናይቱ አንካራ በሚገኘው ቤተ መንግስት ስነ-ስርዓት ላይ ይታደማሉ።
የቱርክ የረጅም ጊዜ መሪ አሁን በሦስተኛ ጊዜ የስልጣን ዘመናቸው ከፍተኛ የሆነ ፈተና ገጥሟቸዋል ተብሏል።
ይህም የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እና ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለው ውጥረት ነው። ተንታኞች ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለው ውጥረት የበለጠ ሊከር እንደሚችል ሰግተዋል።