በቱርክና ሶሪያ በደረሰው ርዕደ መሬት የሟቾች ቁጥር ከ15 ሺህ በላይ ደረሰ
አደጋው ከደረሰ ሶስተኛ ቀኑን መያዙን ተከትሎም በህይወት የሚገኙ ሰዎች ቁጥር እንደሚመናመን ይጠበቃል
ከ70 በላይ ሀገራት ግን ባለሙያዎቻቸውን በመላክ እና የአስቸኳይ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን ቀጥለዋል
በቱርክና ሶሪያ በደረሰው ርዕደ መሬት የሟቾች ቁጥር ከ15 ሺህ በላይ መድረሱ እየተነገረ ነው።
እስካሁን በቱርክ ብቻ ከ12 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተረጋገጧል።
በሶሪያ ደግሞ 3 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በርዕደ መሬቱ ምክንያት መሞታቸውን ሳና የተሰኘው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስነብቧል።
ከ54 ሺህ በላይ ሰዎችም አነስተኛ እና ከባድ ጉዳት እንደገጠማቸው የአለም ጤና ድርጅት መረጃ አመላክቷል።
በአደጋው በርካታ ህፃናት ህይወታቸው ማለፉንም ነው የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ያስታወቀው።
በሺዎች የሚቆጠሩ ህንፃዎችን ያፈራረሰው ርዕደ መሬት አሁንም በርካታ ሰዎችን በፍርሰራሽ ውስጥ ደብቆ እንደያዘ ነው።
ቱርክ ከ12 ሺህ በላይ የአደጋ ሰራተኞች እና ከ9 ሺህ በላይ ወታደሮችን በነፍስ አድን ዘመቻው አሰማርታለች።
ከ70 በላይ ሀገራትም ባለሙያዎቻቸውን በመላክ እና የአስቸኳይ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን ቀጥለዋል።
ይሁን እንጂ አደጋው ከደረሰ 72 ስአታት ያለፉት በመሆኑ በህይወት የሚገኙ ሰዎች ቁጥር እየተመናመነ እንደሚሄድ ይታመናል።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት አደጋ አጋጥሞ በ24 ስአት ውስጥ የሚደረግ የነፍስ አድን ስራ 74 በመቶ ህይወትን የመታደግ እድል አለው።
በሶስት ቀናት ውስጥ በፍርስራሽ ውስጥ ያለን ሰው የማትረፍ እድሉ ወደ 22 በመቶ ፤ በ5 ቀናት ውስጥ ደግሞ ወደ 6 በመቶ ያሽቆለቁላል።
በቱርክም ሆነ በሶሪያ ከዚህ በኋላ የሚደረጉ የነፍስ አድን ስራዎችም ስኬታማነታቸው አነስተኛ እንደሚሆን ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ቱርክን ከ50 ቢሊየን ዶላር ያሳጣል የተባለው ርዕደ መሬት ያስከተለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመቀነስ ሀገራት ድጋፍ ማድረግ ላይ እንዲበረቱም ጥሪ እየቀረበ ነው።