
በወፍ ጉንፋን ምክንያት የ12 እንቁላል ዋጋ አምስት ዶላር ደርሷል
ቱርክ 700 ኮንቴይነር እንቁላል ወደ አሜሪካ ለመላክ ተስማማች።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ሀያል ሀገር አሜሪካ በወፍ ጉንፋን ወረርሽኝ ምክንያት የእንቁላል እጥረት አጋጥሟታል።
በሀገሪቱ ያጋጠመው የወፍ ጉንፋን እንቁላል እና የዶሮ ስጋ አቅራቢዎች ምርቶቻቸውን ለማስወገድ ተገደዋል።
አሜሪካ ባለፉት ሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ በተደጋጋሚ ባጋጠመው የወፍ ጉንፋን ምክንያት 162 ሚሊዮን ጫጩቶችን እንዲወገዱ ተደርገዋል።
ወረርሽኙን ተከትሎም በአሜሪካ አንድ ደርዘን ወይም 12 እንቁላል በአምስት ዶላር እየተሸጠ ሲሆን የ62 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አጋጥሟል።
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ይህን የእንቁላል ዋጋ መናር ለማስተካከል ሲባል ከቱርክ ጋር ስምምነት ፈጽሟል።
በዚህ ስምምነት መሰረት ቱርክ ለአሜሪካ 15 ሺህ ቶን ወይም 700 ኮንቴይነር እንቁላል ለማቅረብ ተስማምታለች ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የወፍ ጉንፋኑ እስካሁን አንድ ዶሮ አርቢ አሜሪካዊን ከመገደሉ ባለፉ በሰው ላይ የጤና ጉዳት አላደረሰም ተብሏል።
የአሜሪካ እንቁላል ዕጥረቱን ካባባሰው ምክንያት መካከል በኢለን መስክ የሚመራው አዲሱ የመንግስት ተቋማት አቅም ግንባታ ወይም በምህጻረ ቃሉ ዶጅ ተብሎ የሚጠራው ተቋም በስህተት ሰራተኞችን ማሰናበቱ እንደሆነ ተገልጿል።
ዶጅ የሚባለው አዲሱ ተቋም የመንግስትን ወጪ ለመቀነስ በሚል በስህተት የአስቸኳይ አገልግሎት ሰጪ ሰራተኞችን ማሰናበቱ የእንቁላል ፍላጎትን አንሯል ተብሏል።