የቱርክ ፍርድ ቤት በማጭበርበር ወንጀል የተከሰሰውን ግለሰብ በ45 ሺህ 370 ዓመት እስር ቀጣ
መህመት አይዲንና ወንድሙ ፋርም ባንክ በሚባል ተቋማቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አጭበርብረዋል

መህመት አይዲን ከ130 ሺህ በላይ ቱርካውያ 131 ቢሊየን የቱርክ ሊራ ተቀብለዋል በሚል ተከሷል
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገንዘብ በማጭበርበር የተከሰሰው የቱርክ የፋርም ባንክ መስራች መህመት አይዲን በ45 ሺህ 376 አመት ከ6 ወር እስራት ተቀጣ።
መህመት አይዲን "ፋርም ባንክ" በሚል በኦንላይን በመሰረተው ተቋም ስም ሰዎች በምናብ እንስሳትን እና ሰብሎችን እንዲገዙ በማድረግ ገንዘብ አጭበርብሯል ተብሏል።
“ቶሱንኩክ” በሚል ቅጽ ስሙ የሚታወቀው መሃመት አይዲን ፋርም ባንክ በሚል የማጭበርበሪያ ድርጅቱ በኩል ከ130 ሺህ ሰዎች ከ131 ቢሊየን የቱርክ ሊራ በላይ ገንዘብ ሰብስቧል ነው የተባለው።
አይዲን ገንዘቡን ከሰበሰበ በኋላ የተወሰነ ገንዘብ በመያዝ በ2018 ከሀገር የወጣ ቢሆንም፤ በፈረንጆቹ 2021 ላይ በብራዚል በቁጥጥር ስር ውሎ ለቱርክ ተላልፎ እንደተሰጠም ነው የተነገረው።
ፋርም ባንክ የኦንላይን የማጭበርበሪያ ጨዋታው በፈረንጆቹ 2016 ላይ ተከፍቶ በ2018 የተዘጋ ሲሆን፤ የክስ ሂደቱ ደግሞ በ2019 ተጀምሯል።
አቃቤ ህግ መህመት አይዲን እና ወንድሙ ፋቲህ አይዲን ህገወጥ ድርጅት በማቋቋም እና በማስተዳደር፣ በማጭበርበር እና በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ከ75 ሺህ ዓመታት በላይ እስራት እንዲቀጡ ጠይቀው ነበር።
መህመት አይዲን ባሳለፍነው ሰኞ በዋለው ችሎት ላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ የተከራከረ ሲሆን፤ “ማንንም ለማታለል አላሰብኩም፤ የማጭበርበር አላማ አልነበረኝም” ሲል ተናግሯል።
“ንብረቶቹን እንዳያንቀሳቀስ እግድ መጣሉም ለተጎጂዎች ካሳ እንዳይከፍል እንዳደረገው” በመግለጽ፣ በተያዘው ገንዘብ ላይ የተጠራቀመው ወለድ የደረሰውን ጉዳት ሊሸፍን እንደሚችል ጠቁሟል።
የመህመት አይዲን ወንድም የሆነው ፋቲህ አይዲን "እኔ የድርጅቱ መስራችም አባልም አይደለሁም፤ አብዛኞቹ ከሳሾ እኔን አያውቁኝም ስለዚህም በነጻ መለቀቅ አለብኝ" ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።
የቱርክ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከተመለከተ በኋላ መህመት አይዲን እና ወንድሙ ፋቲህ አይዲን እያንዳንዳቸው በ45 ሺህ 376 አመት ከ6 ወር እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
ከእስር በተጨማሪም የ496 ሚሊየን የቱርክ ሊራ የገንዘብ ቅጣት ውሳኔም ያሳለፈ ሲሆን፤ ገንዘቡን በ24 ወራት ጊዝ ውስጥ እንዲከፍሉም ትእዛዝ ሰጥቷል።