የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ኤምሬትስ ገቡ
ፕሬዝዳንቱ በአለም የመንግስታት ጉባኤ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን፥ በጋዛ ጉዳይ ከኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ጋር ይመክራሉ
ኤርዶሃን በነገው እለትም በግብጽ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገልጿል
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ለይፋዊ ጉብኝት አረብ ኤምሬትስ ገብተዋል።
ኤርዶሃን በቆይታቸው ከኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ጋር ምክክር ያደርጋሉ።
መሪዎቹ ከሁለትዮሽ ጉዳዮች ባሻገር በጋዛ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ እንደሚወያዩም ነው የተገለጸው።
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ቱርክ፣ ህንድና ኳታር በክብር እንግድነት በተጋበዙበት የ2024 የአለም መንግስታት ጉባኤ ላይም ንግግር ያደርጋሉ ብሏል አናዶሉ በዘገባው።
በነገው እለትም ወደ ካይሮ በማቅናት ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የሚያደርጉት ምክክር ይጠበቃል።
እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት በተደጋጋሚ የኮነኑት ኤርዶሃን ከቴል አቪቭ ጋር ቃላት መወራወር ከጀመረች ዋል አደር ካለችው ግብጽ ፕሬዝዳንት ጋር የሚያደርጉት ምክክር በዋናነት በጋዛ ሁኔታ እንደሚያተኩር ቢጠበቅም የሁለትዮሽ የንግድና ፖለቲካዊ ጉዳዮችም ይነሳሉ ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከግብጽ ጋር ወደምትዋሰነው የጋዛዋ ራፋህ እግረኛ ጦር አዘምታለሁ ማለታቸውና በተከታታይነት የቀጠለው የአየር ድብደባ አንካራና ካይሮን አስቆጥቷል።
ፕሬዝዳንት አብዱልፈታል አልሲሲ ግብጽ ከ40 አመት በፊት ከእስራኤል ጋር የደረሰችውን የሰላም ስምምነት ልንቀድ እንችላለን ሲሉ ዝተዋል።
እስራኤል በራፋህ በተጠለሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን ላይ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት ያወገዙት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶሃንም፥ ቴል አቪቭ በንጹሃን ላይ መሰል ጥቃት ለማድረስ ወኔውን ያገኘችው “በምዕራባውያን እስስታዊ ፖሊሲ” ምክንያት ነው ብለዋል።
“ምዕራባውያን እስራኤል ውጥረት እንድታረግብ በይፋ ሲጠይቁ የኔታንያሁን ወንጀሎች ለማየት አይናቸው ይከደናል፤ ሃማስን ተጠያቂ እያደረጉ ያልፏቸዋል” ሲሉም ተደምጠዋል።
ኤሮዶሃን እና አል ሲሲ በነገው እለት ሲገናኙ ከጋዛው ጦርነት ባሻገር ከ10 አመት በኋላ ዳግም በመታደስ ላይ ያለውን የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ተገልጿል።