መልክሽ ለቴሌቪዥን አይመጥንም የተባለችው እንስት ዝነኛ የኪነ ጥበብ ሽልማቶችን አሸነፈች
ሃና ዋዲንግሀም ጌም ኦፍ ትሮንስን ጨምሮ በበርካታ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ለመሳተፍ በቅታለች
ተዋናይቷ በመምህሯ አንገቷን እንድትደፋ ጥረት እንደተደረገባት እና በጥረቷ ስኬታማ መሆኗን ተናግራለች
መልክሽ ለቴሌቪዥን አይመጥንም የተባለችው እንስት ዝነኛ የኪነ ጥበብ ሽልማቶችን አሸነፈች፡፡
በዓለማችን በሚተላለፉ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማዎች እና ፊልሞች ላይ የምትተውነው ሃናህ ዋዲንግሀም ባንድ ወቅት በመልኳ ምክንያት ጫናዎች ይደርሱባት እንደነበር ተናግራለች፡፡
በየዓመቱ በሚካሄደው የኤሚ የኪነ ጥበብ ሙያተኞች ሽልማትን ያሸነፈችው ሃናህ የ49 ዓመት እድሜ ያላት እና በበርካታ ቲያትሮች እና ተከታታይ ድራማዎች ላይ በመተወን ትታወቃለች፡፡
የኤሚ አዋርድን ከሰሞኑ ያሸነፈችው ይህች እንግሊዛዊት ተዋናይ ባንድ ወቅት መምህሯ በመልኳ ምክንያት ታሸማቅቃት እንደነበር ተናግራለች፡፡
መምህሬ መልኬ ለተሌሌቪዥን እንደማይሆን እና በሌላ ሙያ ላይ ባተኩር እንደሚሻል፣ ፊቴ በስትሮክ የተመታ እንደሚመስል በመንገር ከፍላጎቴ ውጪ በሆነ ሙያ ላይ እንድሰማራ ጫና ይደረግብኝ ነበር ብላለች፡፡
ተዋናይቷ ተወዳጁ ጌም ኦፍ ትሮንስ፣ አፕል ቲቪ ላይ የሚተላለፈው ቴድ ላሶ የተሰኘው ተከታታይ አስቂኝ ድራማን ጨምሮ በበርካታ የዓለማችን ፊልሞች ላይ ተውና ተወዳጅነትን እና ሽልማቶችን አግኝታለች፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በለንደን እና ኒዮርክ ከሚካሄዱ የመድረክ ላይ ትያትሮች ባለፈ በአውሮፓ በሚካሄዱ የኪነ ጥበብ ዝግጅት መድረኮችን በመምራትም ዝነኛ ሆናለች፡፡
መምህሬ ስለ እኔ ያላትን የተሳሳተ አመለካከት ማስቀየር የምችለው ጠንክሬ በመስራት እና ፍላጎቴን እውን በማድረግ መሆኑን ስለማውቅ ይህ እንዲሆን ብዙ ለፍቻለሁ ስትል ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቃለ መጠይቅ ወቅት ተናግራለች፡፡
ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ለማሳካት ወይም የሚወዱትን ነገር መሆን የሚጠበቅባቸው መጣር ብቻ ነው የምትለው ተዋናይት ሀናህ ከህልማችሁ ማንም ሊያስቆማችሁ አይችልም ብላለች፡፡
ተዋናይት ሀናህ መልኳን አስመልክቶ በመምህሯ የተነገራት ነገር ብዙ ነገሮች እንዲወሳሰቡባት አድርጎባት እንደነበርም በቃለ መጠይቁ ወቅት ገልጻለች፡፡
ተዋናይቷ ከኤሚ ኪነ ጥበብ ሽልማቶች በሁለት ዘርፍ አሸናፊ የሆነች ሲሆን በቴሌቪዥን ምርጥ ተዋናይ እና የተመልካቾች ምርጥ ሽልማትን ማሸነፍ ችላለች፡፡