የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ግጭቱን ለመፍታት ብቸኛው መንገድ ተኩስ አቁሞ መደራደሩ ነው ብለዋል
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ ግጭት ተፋላሚ ወገኖችን ለማሸማገል የጀመሩት ጥረት እንደሚቀል የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ፡፡
የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ግጭቱን ለመፍታት ብቸኛው መንገድ ተኩስ አቁሞ መደራደሩ ነው ብለዋል፡፡
ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ይህን ያሉት ትናንት ሃሙስ ህዳር 23 ቀን 2014 ዓ/ም የዓለም የሰላም ተቋም (IPI) የአፍሪካን ወቅታዊ የጸጥታ እና ደህንነት ሁኔታ በተመለከተ በአሜሪካ ኒውዮርክ አዘጋጅቶት በነበረና በበይነ መረብ ጭምር በተላለፈ የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡
በውይይቱ በተቋሙ (IPI) ፕሬዝዳንት ለተነሱላቸው ዓይነተ ብዙ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ሙሳ ፋኪ የኢትዮጵያው ግጭት ቢቀጥልም ከተዋናዮቹ ጋር መነጋገራቸውን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካያቸው አድርገው የሾሟቸው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የጀመሩትን የሽምግልና ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ኮሚሽን ሊቀመንበሩ የተናገሩት፡፡
በቅርቡ ወደ መቀሌ አቅንተው ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር መወያየታቸውን የገለጹት ኦባሳንጆ ከኦሮሚያ እና አማራ ክልል ባለስልጣናት ጋር አበረታች ውይይት ማድረጋቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
በግጭቱ ተዋንያን መካከል ያለው ዋና ልዩነት፤ “የሰላም መንገዱ ምን ይሁን የሚል ነው” ሲሉ መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡
ኦባሳንጆ ወደ መቀሌ አቅንተው ከተመለሱ በግጭቱ ዘርፈ ብዙ ለውጦች ተስተውለዋል፡፡
እስከ ሰሜን ሸዋ ደጋማ አካባቢዎች ዘልቆ የነበረው የህወሓት ተዋጊ ኃይል ጉዞው ከመገታቱም በላይ ለቀጣይ ድሎች ማስፈንጠሪያ የሚሆን ድል ተመዝግቧል እንደ መንግስት ሰሞነኛ መግለጫ፡፡
የህወሓት ተዋጊዎች ጠንካራ ይዞታ የነበሩ ጋሸናን መሰል ግንባሮች መሰበራቸውንና ላሊበላን ጨምሮ መዘዞ፣ ሞላሌ እና ሸዋ ሮቢት ነጻ መውጣታቸው መገለጹም የሚታወስ ነው፡፡
ጦሩ ዛሬን ጨምሮ ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ሌሎች አካባቢዎችን እንደሚያስለቅቅ ከጃማ ደጎሎ ግንባር ሆነው ትናንት በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጦርነቱን መንግስት ማሸነፉ የማይቀር እንደሆነ በማስታወስ የህወሓት ታጣቂዎች እጃቸውን ለጸጥታ አካላት እንዲሰጡ ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡