በአንዲት ግለሰብ ላይ ድብደባ የፈፀሙ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ
የፖሉስ አባላቱ ጉዳያቸው እየተጠራ እንደሚገኝም የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል
በድርጊቱ በተሳተፉት ላይ ህጉን ተከትሎ በማጣራት ተገቢው የእርምት እርምጃ ይወሰዳል- የሰላም ሚኒስት ወ/ሮ ሙፍሪሃት ካሚል
ከፖሊስ የሙያ ስነ-ምግባር ውጪ በአንዲት ግለሰብ ላይ ድብደባ የፈፀሙ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ውለው ምርመራ እየተጠራባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዳስታወቀው ድርጊቱ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው ሚካኤል አደባባይ አካባቢ መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 5፡00 ሰዓት አካባ ነው የተፈጠረው።
ም/ኢ/ር ጃፋር አሊ እና ኮንስታብል መስፍን በተለ የተባሉ የቆሬ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አባላት አንዲትን ግለሰብ “በአስነዋሪ ሁኔታ” በመደብደባቸው በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጠራ እንደሚገኝም ፖሊስ አስታውቋል።
ህዝብን በሰብአዊነት ማገልገል የአዲስ አበባ ፖሊስ መርህ መሆኑ እየታወቀ ነገር ግን አንዳንድ አመራሮችና አባላት ይህን መርህ በመተላለፍ የሚፈፅሙት ህገ-ወጥ ድርጊት ተቋሙ የማይታገስ መሆኑን ገልፆ በ2013 የበጀት ዓመት ብቻ እንኳን በልዩ ልዩ ጥፋት ላይ የተገኙ 171 የፖሊስ አመራሮችና አባላት ከሰራዊቱ እንዲሰናበቱ ማድረጉን ገልጿል
ከስራ ከተሰናበቱት 29ኙ ከሰብአዊ መብት ጥስት ጋር በተያያዘ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልፆል።
የሰላም ሚኒስት ወ/ሮ ሙፍሪሃት ካሚል በበኩላቸው፤ “በርካታ ዜጎቻችን ልብ የሚሰብር የቪዲዮ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ሲቀባበሉ ተመልክተናል” ብለዋል።
“በድርጊቱ የተሳተፉ ሁለት የፓሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል” ያሉ ሲሆን፤ ህጉን ተከትሎ የማጣራትና ተገቢው የእርምት እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።
በዚህ አጋጣሚ ዜጎች ለሰብዓዊ መብት መከበር እንዲህ አይነት ህገወጥ ተግባራትን በመከታተልና በማጋለጥ ረገድ ማህበራዊ ሚዲያን አዎንታዊ ለሆነ ተግባር ማዋል መቻላቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።