ሁለት ቢሊየን የዓለም ህዝብ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ይኖራል- ተመድ
የዩክሬኑ ጦርነት 10 ሚሊየን ህዝብ ከቤቱ እንዲፈናቀል አድርጓል ተብሏል
ከ 270 ሚሊየን በላይ ሕዝብ በዚህ ዓመት ድጋፍ ይፈልጋል ተብሏል
ከዓለም ሕዝብ ሁለት ቢሊየን የሚሆነው ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች እየኖረ መሆኑ የተባሩት መንግስታት ድርጅት ተገለጸ።
የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ከዓለም ሕዝብ ሩብ ያህሉ በጦርነት ቀጠና ውስጥ እንደሚኖር አስታውቀዋል። ዋና ጸሐፊው በየመን፣ በሶሪያ፣ በሚያንማር፣ በሱዳን፣ በሄይቲ እና በሳህል አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን በአብነት አንስተዋል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሁከትን የፈጠሩ ከፍተኛ ግጭቶች አሁን ላይ መስተዋላቸው ተገልጿል።
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በየመን፣ በሶሪያ፣ በሚያንማር፣ በሱዳን፣ ሄይቲና ሳህል ቀጠና ያሉ ጦርነቶች እንዲሁም የቅርብ ጊዜው የዩክሬኑ ጦርነት ዓለም የተገነባበትን ስርዓት የሚሸረሽሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
እነዚህ ጦርነቶች በምግብ፣ በነዳጅና በማዳበሪያ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዲኖር ምክንያት እንደሆኑም ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ 84 ሚሊየን ሰዎች ጦርነት በፈጠረው ሁከትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ቤታቸውን ለቀው መሰደዳቸውን ተመድ ገልጿል።
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የተደረገው ጦርነትም 4 ሚሊዮን ዜጎችን ከዩክሬን ሲያስወጣ በሀገሪቱ ውስጥ ደግሞ 6 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚሆኑት እንዲፈናቀሉ አድርጓል ነው የተባለው።
በዚህ ዓመት ብቻ 274 ሚሊየን ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚፈልጉ ያነሱት ዋና ጸሐፊው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ 17 በመቶ ጨምሯል ብለዋል።