በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ንግግሮች መቀጠላቸውን የተመድ ም/ዋና ኃሃፊ ገለጹ
ህወሓት በአፋር ክልል ጦርነት መክፈቱን እና ቦታዎች መቆጣጠሩን የአፋር ክልል ገልጿል
ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በአዲስ አበባ የተገኙት የተመድ ምክትል ዋና ፀሀፊ የአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎችን ጎብኝተዋል
በ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ በአማራ፣ በትግራይ እና በአፋር ክልሎች ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
ወደ ኒውዮርክ ከመመለሳቸው ከሰዓታት በፊት የአፋር ክልልን የጎበኙት አሚና መሐመድ በክልሉ ዱብቲ ሆስፒታል በጦርነት የተጎዱ ዜጎችን ተመልክተዋል ተብሏል፡፡
- ህወሓት በሌሎች አካላት በኩል ከመንግስት ጋር ስወያይ ነበር አለ
- ህወሓት “ከመንግስት ጋር በሌሎች አካላት በኩል እየተወያየሁ ነው” ማለቱን መንግስት አስተባበለ
- ህወሓት አንድ የአፋር ዞን ተቆጣጥሮ የኢትዮ-ጅቡቲ መስመርን ለመቁረጥ ውጊያ ከፍቷል- አፋር ክልል
በሰመራ ከተማ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ጋር ውይይት አድርገው ነበር፡፡ አቶ አወል አርባ ለተመድ ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ “ዓለም ለገዳይ ድጋፍ እያደረገ ለተገዳይ ድምጽ የማይሆንበት ምክንያት ምንድነው፤ ዓለም ወራሪውን እየደገፈ ነው፤ የእናንተ አመጣጥ ለወራሪው በር ለመክፈት ነወይ” የሚል ጥያቄ ለተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አንስተዋል ተብሏል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉት የአፋር የሀገር ሽማግሌ ሀቢብ መሀመድ ያዮ “ግን እኛ ግን ጦርነት ውስጥ ነን” ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ደግሞ ህወሀት በአፋር ህዝብ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲሁም የጅምላ ግድያ፣ ግፍና ሰቆቃ እያደረሰ ነው ብለዋል፡፡
ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ ከሰመራ ከተመለሱ በኋላ በሰጡት መግለጫ በመንግስት እና በህወሃት ኃይሎች መካከል ስላለው የሰላም ንግግር ተጠይቀው ነበር፡፡ የተመድ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴርዝ የሰላም ሂደቶች በአፍሪካ ሕብረት በኩል መቀጠላቸውን መግልጻቸውን ተከትሎ አሁን በዚሁ ዙሪያ አዲስ ነገር ይኖር እንደሆነ የተጠየቁት አሚና መሐመድ የአፍሪካ መሪዎች ጭምር ከመንግስት ጋር ሰላምን በተመለከተ መነጋገራቸውን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የሰላም ንግግሮች መቀጠላቸውን ያነሱት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ ከወራት በፊት ከነበረው አንጻር አሁን ግጭቱ መቀነሱን አንስተዋል፡፡ አሁንም ንግግሮቹ ቀጥለዋል ያሉት አሚና መሐመድ የተሻለ ንግግር መደረጉንና ብሔራዊ ምክክሩ በራሱ ወደ ሰላም የሚወስድ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የህወሃት አመራሮች ፍላጎት ምን እንደሆነ የተጠየቁት አሚና መሐመድ የህወሃት አመራሮች ፍላጎት በሁሉም ወገኖች እንደሚታወቅ አንስተው የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲገባ፤ ተኩስ እንዲቆምና ንግግር እንዲጀመር ፍላጎት አላቸው ብለዋል፡፡
ምንም እንኳ ምክትል ዋና ፀሐፊዋ ንግገሮች መኖራቸውን ቢገልጹም የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ግን ህወሀት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በአፋር ንፁሀን አርብቶ አደሮች ላይ የዘር ማጥፋት እያካሄደ መሆኑን ገልጸውላቸዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት የቀንዱ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እና የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሁን ላይ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሃት ሃይሎች መካከል ንግግሮች እንዲደረጉ ጥረቶች እየተደረጉ ስለመሆናቸው እየገለጹ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉ ያሉት ሁለቱ ናይጀሪያውያን አሁን ያለው ሁኔታ የተሻለ ስለመሆኑ እየገለጹ ቢሆንም አሁንም ግን ጦርነት እየተደረገ ነው፡፡
በመንግስት በሽብር ወንጀል የሚፈለጉት የህወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ከሳምንታት በፊት ከመንግስት ጋር ንግግር መጀመሩን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው ከህወሃት ጋር የተጀመረ ንግግር እንደሌለ ለአል ዐይን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡