መንግስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ የመንግስት የስልጣን እርከኖች እንደሚወከሉ ገልጿል
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ(አዴሃን) አመራሮች በአዲሱ የአማራ ክልል ካቢኔ ውስጥ ተካተው በዛሬው እለት ተሾመዋል።
ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በክልሉ አብላጫ ድምጽ ያገኘው፣ የአማራ ብልጽግና በዛሬው እለት ክልሉን ለቀጣይ አምስት አመታት የሚመራ አዲስ መንግስት መስርቷል።
አዲሱ የክልሉ ምክር ቤት፤ የአማራ ክልል ትምህርት ቤሮ ኃለፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነሩትን ይልቃል ከፋለን(ዶ/ር) የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አድርጎ የሾመ ሲሆን፤ ቃለ መሃላም ፈፅመዋል።
ክልሉን ለመምራት ስልጣን ከቀደሞው ርእስ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የተረከቡት ይልቃል(ዶ/ር) በክልሉ የተፈጠረውን ችግር እንደሚፈቱ ቃል ገብተዋል።
በክልሉ ሹመት ያገኙት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አቶ ጣሂር መሀመድ ከአብን እና አቶ ተስፋሁን አለምነህ ከአዴሃን ናቸው።
የአብን የህዝብ ግኝኑት ኃላፊ አቶ ጣሂር ሙሃመድ የክልሉ የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ፤ የአዴሃኑ አቶ ተስፋሁን አለምነህ ደግሞ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ሆነው ተሾመዋል።
አዲስ የተመሰረተው የአዲስ አበባ ከተማ መንግስትም ለሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ሹመት መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህም የአብኑ የሱፍ ኢብራሂም የንብረት አስተዳደር ባለስለጣን፤ የኢዜማው አቶ ግርማ ሰይፉ ደግሞ የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ በመሆን ተሾመዋል።
ነገርግን አቶ የሱፍም ሆነ፤ አቶ ግርማ ሰይፍ በሹመቱ ዙሪያ ያሉት ነገር የለም።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በቅርቡ በነበራቸው ቆይታ በአዲሱ የፌደራል መንግስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ወኪሎች ሃሳባቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበት፤ በተለያዩ የመንግስት እርከኖች ውስጥ የሚሳተፉበት እድል እንደሚኖር መናገራቸው ይታወሳል።
በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ፤ ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ድምጽ ማግኘቱንና ሌሎች ሶስት ተቀዋሚ ፖርቲዎች የፓርላ መቀመጫ ማሸነፋቸውን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።
ጠቅላላ ምርጫው በተለያየ ምክንያት በሁሉም የምርጫ ክልሎች መካሄድ ባይችልም፣ ምርጫ ቦርድ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ መገኘቱን ይፋ አድርጎ ነበር። የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትም መስከረም 24 አዲስ መንግስት እንደሚመሰረት አስታውቋል።