በአማራ ክልል አራት ሚሊዬን ዜጎች ችግር ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ
አራት ሚሊዮን ያህል ሕዝብ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ አገኘሁ፤ ዩኒሴፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል
ርዕሰ መስተዳድሩ በሽብርተኛነት የተፈረጀው ህወሓት “በወረራቸው” አካባቢዎች ግማሸ ሚሊዬን ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል
በአማራ ክልል በህወሓት “ወረራ” ምክንያት አራት ሚሊዬን ዜጎች ችግር ውስጥ መሆናቸውን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አገኘሁ ተሻገር ከተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ማዕከል (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ኃላፊ አዴል ከድር ጋር በባህር ዳር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መወያየታቸው ተገልጿል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት “በወረራቸው” አካባቢዎች ግማሸ ሚሊዬን ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጸው፤ አራት ሚሊየን የሚደርሱት ደግሞ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ህወሓት አሁን ላይ በሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ዋግኸምራ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ግማሽ ሚሊዮን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉን የገለጹት አቶ አገኘሁ፤ ከክልሉ ሕዝብ አራት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
ህወሓት በገባባቸው የክልሉ አካባቢዎች ማህበራዊ ተቋማት በተለይም ትምህርት ቤቶች እና ጤና ተቋማትን ማውደሙንና ዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈፀሙንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡
ዩኒሴፍ ይህንን አስከፊ ችግር ለመቋቋም የሚያስችል አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም አቶ አገኘሁ ጠይቀዋል፡፡
አቶ አዴል ከድር በሰሜን ጎንደርና አካባቢው ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸው በርካታ ህፃናት በምግብ እጥረት “ፈታኝ” ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በውይይቱ ላይ አንስተዋል፡፡
ታዳጊዎች በመጭው የትምህርት ዘመን በትምህርት ገበታ ለመታደም አሳሳቢ ሁኔታ እንዳለ ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ በቀጣይ ጊዜያት ወደ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች እንደሚጓዙም ተናግረዋል፡፡
ከተባበሩት መንግስታት እህት ድርጅቶችና ከሌሎች ረድኤት ድርጅቶች ጋር በመሆን ችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች በአፋጣኝ እርዳታ እንዲደርሳቸው እንሰራለን ብለዋል፡፡
ዩኒሴፍ “ወረራ” ምክንያት ለተፈናቀሉ እና ችግር ላይ ለወደቁ ዜጎች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡