አውሮፕላኖቹ በዳላስ የአየር ላይ ትዕይንት በማሳየት ላይ እንደነበሩ ተገልጿል
አሜሪካ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት እንድታሸንፍ የረዱ ሁለት አውሮፕላኖች በአየር ላይ መጋጨታቸው ተገለጸ፡፡
በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ዳላስ ከተማ የአውሮፕላን ትዕይትንት ስነ ስርዓት ለታዳሚዎች በመካሄድ ላይ ሲሆን ዋሸንግተን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጠቀመቻቸው የጦር አውሮፕላኖች የበረራ ትዕይንት ለታዳሚዎች በማቅረብ ላይ ነበሩ፡፡
አሜሪካ የጀርመን ናዚ ጦር ላይ ድል የተቀዳጀችበት ቦይንግ ቢ-17 የተሰኘው የጦር አውሮፕላን ከተጋጩት አውሮፕላኖች መካከል አንዱ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሁለተኛው አውሮፕላን ደግሞ ፒ-63 ኪንግ ኮብራ የሚሰኝ ሲሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ አሜሪካንን በሚገባ እንዳገለገለ ሲገለጽ የሶቪየት አየር ሀይልን ለመመከት መዋሉ ተገልጿል፡፡
ቴሪ ባርከር እና ሌን ሩት የተሰኙት የጦር አውሮፕላኖቹ አብራሪዎች ህይወታቸው ወዲያውኑ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን የአሜሪካ አቪዬሽን አስተዳድር አደጋውን እንደሚመረምር አስታውቋል፡፡
አውሮፕላኖቹ የበረራ ትዕይንት በማሳየት ላይ እያሉ እርስ በርስ ተጋጭተው ወደ ምድር ወርደው ተከስክሰዋል የተባለ ሲሆን አደጋው እንደተፈጠረ ወዲያውኑ በእሳት እንደተያያዙ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይህ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ኤር ሾው ካሳለፍነው አርብ እስከ ዛሬ ድረስ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን፣ አደጋው ሲደርስ እስከ 6 ሺህ ሰዎች እየተመለከቱት እንደነበር ተገልጿል፡፡
በዚህ የአውሮፕላኖቹ አደጋ ከአብራሪዎቹ ውጪ በተመልካቾቹ ላይ ምንም አይነት አደጋ አለመድረሱ ሲገለጽ አደጋው ሰቅጣጭ እንደነበር የዳላስ ከንቲባ ተናግረዋል፡፡