ኬንያና ሶማሊያ በንግድና የዲፕሎማሲ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ
ሰምምነቱ ሶማሊያ ወደ ኬንያ ዓሳ መላክ እንድትልክ እንዲሁም ኬንያ ወደ ሶማሊያ ጫት መላኳን እንድትቀጥል የሚያስችል ነው
በሀገራቱ መካከል የተደረሰው ስምምነት ሻክሮ ነበረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያሻሽል ተብሎለታል
ኬንያ እና ሶማሊያ በንግድ እና የዲፕሎማሲ ዘርፍ አብሮ ለመስራት የሚያስችልዋቸው ስምምነቶችን መፈራረማው ተነግሯል።
ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በናይሮቢ የሚገኙት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከኬንያው አቻቸው ጋር በመንግስታት ደረጃ አብሮ ለመስራት የሚያስችልዋቸው ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
ሁለቱ ሀገራት በተፈራረሙት የንግድ ስምምነት መሰረት ሶማሊያ ወደ ኬንያ ዓሳ መላክ እንድትጀምር እንዲሁም ኬንያ ወደ ሶማሊያ ጫት መላኳን እንድትቀጥል የሚያስችል ነው።
የኬንያ አየር መንገድ ወደ ሞቃዲሾ የሚያደርገው በረራም ቀደም ሲል በነበረው የአየር ትራፊክ ስምምነት መሰረት እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በተጨማሪም በሀገራቱ መካከል የተፈረመው የዲፕሎማሲ ስምምነት ሁለቱ ሀገራት በ10 የስራ ቀናት ውስጥ መደበኛ የሶማሊያ ፓስፖርት የያዙ የቪዛ የሚገኙበት ሁኔታ ለማመቻቸት እንዲሁም ለዲፕሎማቶች እና የሶማሊያን ሰርቪስ ፓስፖርት የያዙ የናይሮቢ ቪዛን በነጻ የሚያገኙበት ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን የኬንያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በማህበራዊ የትስስር ገጹ ላይ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
በቅርቡ በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ የሹመት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበዓለ ስሜቱ ላይ ባደረጉት ንግግር "ሰላምና የበለጸገች የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ማየት የሁሉም ኬንያዊ ህልም ነው" ሲሉ ለሶማሊያ ያላቸውን መልካም ምኞት መግለጻቸው አይዘነጋም።
"በኬንያ ያሉ ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ፣ ሁላችንም በኢኮኖሚ እንድንጠቀም እና አብረን እንድንበለጽግ ከእናንተ ጋር ለመስራት በጉጉት እንጠባበቃለን" ሲሉም ተናግረው ነበር።
ይህን ተከትሎም ላለፉት ሁለት አመታት በኬንያ ጫት ላይ እገዳ ጥላ የነበረችው ሶማሊያ እገዳውን ልታነሳ መሆኑ መግለጿ የሚታወስ ነው።