ታዋቂው ቦክሰኛ ማይክ ታይሰን በህዳር ወር ለሚኖረው ፍልሚያ ዝግጅት መጨረሱን ገለጸ
ታይሰን ከ19 አመታት በኋላ ወደ ‘’ሪንግ’’ የሚመለስበት ተጠባቂው የቦክስ ግጥሚያ ከዩቲዩበሩ ጄክ ፖውል ጋር የሚያደርገው ነው
በሰኔ ወር ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ፍልሚያ ታይሰን ባጋጠመው መጠነኛ ህመም መራዘሙ ይታወሳል
የቀድሞው የአለም ቦክስ ሻምፒዮና ማይክ ታይሰን ህዳር 15 ለሚደረገው የቦክስ ፍልሚያ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
ማይክ ታይሰን በ31 አመት ከሚያንሰው የ27 አመቱ ዩትዩበር ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ ሀምሌ 20 ላይ እንዲደረግ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም ታይሰን ባጋጠመው የሆድ ህመም ልምምዱን በማቋረጡ ግጥሚያው ተራዝሞ ነበር፡፡
በህመሙ ምክንያት በሙሉ አቅሙ ልምምዱን እያከናወነ እንዳልሆነ የገለጸው ማይክ ታይሰን ሀኪሞቹ ለትንሽ ሳምንታት እረፍት እንዲያደርግ እና ቀለል ያሉ ልምምዶችን ብቻ እንዲሰራ እንዳሳሰቡት በወቅቱ መናገሩ ይታወሳል፡፡
በትላንትናው እለት ውድድሩ ለህዳር 15 እንደተራዘመ በተገለጸበት መድረክ ታይሰን "ካጋጠመኝ የጤና እክል አገግሜ ልምምዴን በተገቢው መንገድ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡
አክሎም “ለውድድሩ ዝግጁ ነኝ ጄክ ፖውልን በሪንግ ውስጥ እንደሌባ ነው የማሯሩጠው” ሲል ተደምጧል።
ተፋላሚው ጄክ ፖውል በበኩሉ ማይክ ታይሰንን አከብረዋለሁ እስከ ህዳር 15 ግን ጓደኛሞች አይደለንም ብሏል፡፡
ተጋጣሚዎች ፍትሀዊ የሆነ የልምምድ ግዜ እንዲኖራቸው ፣ ሁለቱም ለውድድሩ ዝግጁ እና ብቁ በሆኑበት ግዜ ብቻ ውድድሩን ለማካሄድ ተስማምተዋል።
ውድድሩ እያንዳንዳቸው ሁለት ደቂቃ ርዝማኔ በሚኖራቸው 8 ዙሮች የሚደረግ ሲሆን የውድድሩ አሸናፊ በዝረራ ወይም በዳኞች ውሳኔ የሚለይ ይሆናል፡፡
ፍልሚያው በአርሊንግተን ቴክሳስ 80 ሺህ ሰዎች በሚይዝ ስታድየም ውስጥ እንደሚደረግ ሲገለጽ ፤በተጨማሪም ግዙፉ የፊልም እና መዝናኛ ማሰራጫ ኔትፍሊክስ ውድድሩን ለማስተላለለፍ እየተጠባበቀ ይገኛል።
የ57 አመቱ ማይክ ታይሰን በአለም ላይ በቦክሱ ዘርፍ ስመጥር ከሆኑ ስኬታማ ቦክሰኞች መካከል አንዱ ሲሆን ሶስት የተለያዩ የቦክስ ፍልሚያ ክብሮችን በመቀዳጀት የመጀመርያው የከፍተኛ ሚዛን ቦክሰኛ ነው።
በ1990 በበስተር ዳግላስ ተሸንፎ ከቦክስ አለም እራሱን ያገለለው ታይሰን አነስተኛ የቦክስ ፍልሚያዎችን ሲያደረግ ቆይቷል፡፡ ለመጨረሻ ግዜ የቦክስ ግጥምያ ያደረገው በ2005 በተከናወነ የቦክስ ኤግዝቢሽን ላይ ሲሆን አሁን ወደ ‘’ሪንግ’’ የሚመለሰው ከ19 አመታት በኋላ ነው።
ተፋላሚው ጄክ ፖውል በበኩል ከማይክ ታይሰን በ30 አመት የሚያንስ የ27 አመት ወጣት ዩትዩበር ነው፡፡
ወደ ቦክስ ውድድሩ አለም ከገባ በኋላ ከቀድሞ የዩኤፍሲ ተጋጣሚዎች ጋር 10 ጨዋታዎችን አድርጎ ዘጠኙን ማሸነፍ ችሏል።