አሜሪካ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ለአፍሪካ 55 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እንደምትሰጥ አስታወቀች
ፕሬዝዳንት ባይደን በቀጣይ አፍሪካን እንዲጎበኙ ከበርካታ ሀገራት ግብዣ ቀርቦላቸዋል
ላለፉት ሶስት ቀናት በዋሸንግተን ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ-አሜሪካ የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቋል
አሜሪካ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ለአፍሪካ 55 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እንደምትሰጥ አስታወቀች።
በአፍሪካ እና አሜሪካ መሪዎች መካከል ሲካሄድ የሰነበተው ጉባኤ የተጠናቀቀ ሲሆን አሜሪካ ለአፍሪካ 55 ቢሊዮን ዶላር እንደምትሰጥ አስታውቃለች።
በዚህ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የ49 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ቡርኪናፋሶ፣ ሱዳን፣ ማሊ እና ኤርትራ ደግሞ ዲሞክራሲዊ ስርዓት የላቸውም በሚል በዚህ ጉባኤ ላይ አልተሳተፉም።
የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሽብርተኝነት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ እና ወታደራዊ ትብብሮች የአፍሪካ-አሜሪካ ጉባኤ ዋነኛ አጀንዳዎች ነበሩ።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው ለአፍሪካ 55 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እንደምትሰጥ ገልጸው እርዳታው በቀጣዮቹ ሶሰት ዓመታት ውስጥ ይተገበራል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በተጨማሪም አፍሪካ በቡድን 20 ሀገራት ስብስብ ውስጥ እንድትካተት እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡
ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የጉብኝት ግብዣ እንደቀረበላቸው የተናገሩት ፕሬዝዳንት ባይደን አፍሪካን ለመጎብኘት መጓጓታቸውንም አክለዋል፡፡
የ55 ሀገራት ስብስብ የሆነችው እና ከአንድ ቢሊዮን በላይ የህዝብ ብዛት ያላት አፍሪካ በቡድን 20 ሀገራት ውስጥ ደቡብ አፍሪካ በብቸኝነት እየተሳተፈች ሲሆን ተጨማሪ ሀገራት እንዲካተቱ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ብዙ ሀገራት ሲወተውቱ ቆይተዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደንም በዚህ የቡድን 20 ስብስብ ውስጥ አፍሪካ ተጨማሪ ውክልና ልታገኝ እንደሚገባ ጠቁመው የትኛው ሀገር እንደሚሳተፍ ግን እስካሁን ከመናገር ተቆጥበዋል።
ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስር አሜሪካንን ያሳሰበ ሲሆን በቀጣይ የቤጂንግ ተጽዕኖን መመከት የሚያስችሉ ግንኙነቶች እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ ፕሬዝዳንት ባይደን ጠቁመዋል።
ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላት የንግድ እና ኢንቨስትመንት መጠን አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ካላት ጋር ሲነጻጸር አራት እጥፍ ብልጫ አለው ተብሏል።