በአፍሪካ-አሜሪካ ጉባኤ ዋሽንግተን በቻይና የተወሰደባትን የበላይነት ለመመለስና ተደማጭነቷን ለማስፋት እየሰራች ነው
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባይደን አሜሪካ በአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ 'ሁሌም ዝግጁ ናት' አሉ።
ፕሬዝዳንቱ በንግድና መዋዕለ-ነዋይ ዘርፎች በዩናይትድ ስቴትስ እና በአፍሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ስምምነትን አስተዋውቀዋል።
ማክሰኞ በጀመረው እና ለሦስት ቀናት የዋሽንግተን እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ አሜሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባይደን ከ49 ሀገራት የተውጣጡ መሪዎችና የአፍሪካ ህብረት ኃላፊዎች ጋር በአህጉሪቱ የወደፊት እጣ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ "ሙሉ ለሙሉ አለች" ብለዋል።
የባይደን አስተያየት እና የመሪዎች ጉባኤው አሜሪካ አፍሪካን አጋር ለማድረግ ያለውን አቋም አመላካች መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
- የጋና ፕሬዝዳንት አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ክብርን ለማግኘት ምዕራባውያንን መለመን ማቆም አለባቸው አሉ
- ወደ አሜሪካ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል
ጉባኤው ሀገሪቱ ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ተደማጭነቷን ለማስፋት ከቻይና ጋር ፉክክር ውስጥ በምትገኝበት ወቅት አሜሪካ የአፍሪካ ሀገራት አጋር እንድትሆን ለማድረግ ዓላማ ሰንቃለች ነው የተባለው።
ቻይና ከአፍሪካ ጋር የምታደርገው የንግድ ልውውጥ ከአሜሪካ በአራት እጥፍ ያህል መሆኑን የጠቀሰው ሮይተርስ፤ ቤጂንግ ከምዕራባውያን አበዳሪዎች ይልቅ ርካሽ ብድር በማቅረብ ሁነኛ አበዳሪ ሆናለችም ብሏል።
ባይደን ከአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ጋር የተደረሰው አዲስ ስምምነት የአሜሪካ ኩባንያዎች አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊየን ህዝብ እና ሦስት ነጥብ አራት ትሪሊየን ዶላር የሚገመት ገበያ ያገኛሉ ብለዋል።
በጉባዔው ላይ ስምምነቶችን ያደረጉ ኩባንያዎች የተዘረዘሩ ሲሆን፤ ጄኔራል ኤሌክትሪክ እና ሲስኮ ሲስተምስ ኢንክ የተባሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ይገኙበታል።
ፕሬዝዳንቱ "አፍሪካ ሲሳካላት፤ ዩናይትድ ስቴትስ ይሳካላታል፤ እውነቱን ለመናገር መላው ዓለምም እንዲሁ ይሳካለታል" ብለዋል።
የአፍሪካ-አሜሪካ ጉባኤ በፈረንጆቹ 2014 በቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከተደረገ በኋላ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የመሪዎች ጉባኤ ነው ተብሏል።
አጋርነቱን ለመጀመር የባይደን አስተዳደር 55 ቢሊዮን ዶላር ለምግብ ዋስትና፣ ለአየር ንብረት ለውጥ፣ ለንግድ ሽርክና እና ለሌሎች ጉዳዮች ቃል ገብቷል።
ባይደን አፍሪካ ህብረት የቡድን 20 አባል እንዲሆን የመሪዎች ጉባኤ ላይ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።