የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 103ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
አሜሪካ በሀገሯ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ እንዳይዘጋ መጠየቋ ተሰምቷል።
በሩሲያ የአሜሪካ አምባሳደር ጆን ሱልቪያን፤ ሩሲያ በአሜሪካ የሚገኘው ኤምባሲዋን እንዳትዘጋ አሳስበዋል።
አምባሳደሩ አክለውም አሜሪካ እና ሩሲያ የዓለማችን ኑክሌር አረር ያላቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት ናቸው ግንኙነታቸው በማንኛውም ደረጃ ቢሆን ንግግራቸውን ሊያቋርጡ አይገባም ሲሉም ለሩሲያው ዜና ወኪል ታስ ተናግረዋል።
ምዕራባዊያን የሩሲያውን ታዋቂ ፈላስፋ እና ደረሲ ሊዮ ቶልስቶይ መጽሀፍትን ከቤተ መጽሃፍቶቻቸው ለማውረድ እያደረጉት ያለውን ድርጊት የኮነኑት አምባሳደሩ፤ ሁለቱ ሀገራት መነጋገራቸው ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።
ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመለገስ ላይ ሲሆኑ፤ ሩሲያም የተለገሱትን የጦር መሳሪያዎች በማውደም ላይ መሆኗን ገልጻለች።
ከሰሞኑ ከአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን የተለገሱ የጦር ተሽከርካሪዎችን እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ማውደሟን የሀገሪቱ ዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንዳይለግሱ አሳስበው ልገሳቸውን ከቀጠሉ ግን እርምጃ መውሰዴን እንደሚቀጥሉ አስጠንቅቀዋል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ይፋዊ ጦርነት ከጀመረች 103 ቀናት ሆኖታል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ6 ሚሊየን በላይ ዩክሬናዊያን ዜጎች መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ሲሰደዱ 20 በመቶ የዩክሬን ክፍልም በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ወድቋል።
ጦርነቱን ተከትሎም አውሮፓ ህብረት፣አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦች የተጣሉባት ሲሆን፤ ሩሲያም የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ትገኛለች።