ጠበቃው ትራምፕን የተመለከተ መጽሃፍ ለማሳተም መዘጋጀታቸውን አስታውቀው ነበር
የፕሬዝዳንት ትራምፕ የቀድሞው ጠበቃ ከእስር እንዲለቀቁ ተወሰነ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ ጠበቃ የነበሩት ማይክል ኮኸን ከእስር እንዲለቀቁ የሃገሪቱ የፌዴራል ፍርድ ቤት ወሰነ፡፡
ፍርድ ቤቱ ኮኸን እንዲለቀቁ የወሰነው ፕሬዝዳንት ትራምፕን የተመለከተ መጽሃፍ መጻፋቸውን ተከትሎ በተወሰደባቸው የበቀል እርምጃ መታሰራቸውን በማረጋገጡ ነው፡፡
በመሆኑም ኮኸን ዛሬ ከእስር እንዲለቀቁና በቤታቸው እንዲሄዱ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡
ኮኸን እ.ኤ.አ ከ2006 እስከ 2018 ባሉት 12 ገደማ ዓመታት የዶናልድ ትራምፕ እና የንግድ ተቋማቶቻቸው ጠበቃ በመሆን አገልግለዋል፡፡
ሆኖም ትራምፕ ፕሬዝዳንት ለመሆን ከበቁበት ከ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ ጋር በተያያዘ ተሰሩ በተባሉ ነገር ግን እርሳቸው በትራምፕ ትዕዛዝ አደረግኋቸው ባሏቸው ወንጀሎች ምክንያት ተከሰው 3 የእስር ዓመታትን እንዲያሳልፉ ተፈርዶባቸዋል፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ መቀስቀስ ለህይወታቸው ስጋት መሆኑን በተመለከተ የቀረበለትን አቤቱታ የተቀበለው ፍርድ ቤትም ከእስር ቤት ወጥተው በቤት ውስጥ እስር እንዲቆዩ ባሳለፍነው ግንቦት ወስኖ ነበር፡፡
ሆኖም በቤት ውስጥ የእስሩ ጊዜ ከሚዲያ ጋር እንዳይገናኙ እና ያልተፈቀዱ ተግባራትን እንዳይፈጽሙ የተቀመጡላቸውን ገደቦች በመጣሳቸው በያዝነው የፈረንጆቹ ወር መባቻ ተመልሰው ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ተደርጎ ነበር፡፡
ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ መደረጉ ፕሬዝዳንቱን በተመለከተ የጻፉትን መጽሃፍ ከመታተም ለማስተጓጎል በማሰብ የተፈጸመ እንደሆነ ያቀረቡትን አቤቱታ ያደመጠው ፍርድ ቤት ግን ከእስር ነጻ ሆነው በቤታቸው እንዲቆዩ በድጋሚ ወስኗል፡፡
ጠበቃው በቀጣዩ ዓመት ህዳር ወር ከሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት በወርሃ መስከረም ፕሬዝዳንቱን በተመለከተ አሰናዳሁ ያሉትን መጽሃፍ የማሳተም ውጥን እንዳላቸው የግሎብ ኤንድ ሜይል ዘገባ ያመለክታል፡፡