የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ
ልዩ መልዕክተኛው ዴቪድ ሳተርፊልድ በቅረቡ ከኃላፊነታቸው ሊለቁ እንደሚችሉ መረጃዎች እየወጡ ነው
ከሳተርፊልድ ከኃላፊነት መልቀቅ ጋር ተያይዞ በአሜሪካ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ባዛሬው እለት አዲስ አበባ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
ከምክትላቸው ፔርቶን ክኖፕ ጋር በዛሬው እለት አዲስ አበባ እንደሚገቡ የሚጠበቁት ልዩ መልእክተኛው ሳተርፊልድ፤ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር እንደሚመክሩ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ልዩ መልእከተኛው እና ምክትላቸው ከኢትዮጵያ መንግሰት በተጨማሪ ከሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ተቋማት ተወካዮችና ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አካላት ጋር ይገናኛሉ ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ዴቪድ ሳተርፊልድ በቅርቡ ከኃላፊነታቸው ሊለቁ እንደሚችሉ የዓለም አቀፍ ጉዳዮችና ግንኙነቶችን ትኩረት አድርጎ የሚዘግበው ፎሬይን ፖሊሲ አመላክቷል።
የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት ዴቪድ ሳተርፊልድ ከኃላፊነት መልቀቅ፤ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ አለመራጋጋት፣ የጅምላ ግድያና የረሃብ ስጋት ባለበት ቀጠና ትልቅ የሆነ የዲፕሎማሲ ክፍተት የሚፈጥር ነው ተብለዋል።
ፎሬይን ፖሊሲ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረትም፤ ሳተርፊልድ ከኃላፊነታቸው ሲለቁ ምክትላቸው ፔይቶን ኖፕፍ እሳቸውን ተክተው የሚሰሩ ይሆናል።
ፎሬይን ፖለሲ ይህን ይበል እንጂ፤ ከሳተርፊልድ ከኃላፊነት መልቀቅ ጋር ተያይዞ ለምን እና መቼ በሚሉ ጊዳዮች ላይ እስካሁን በአሜሪካ በኩል የተባለ ነገር እንደሌለ መረጃዎች መረጀዋች ያሳያሉ።
በቱርክ እና ሊባኖስ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ሳተርፊልድ ፤ በሶስት ወራት ቆይታቸው ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ እንዲገባ፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ጊዜያው ግጭት ማቆም እንዲደረግ ተልቅ ግፊት ማድረጋቸው ይነሳል።
ይሁን እንጂ የሳተርፊልድ ከኃላፊነት መልቀቅ፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ እንዲመጣ የምትሻውን ሰላም ሊያደናቅፍ እንደሚችል በርካታ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላትና ባለሙያዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
በአትላንቲክ ካውንስል ጥናትና ምርምር የምስራቅ አፍሪካ ኤክስፐርት የሆኑት ካሜሮን ሃድሰን፤ የልዩ መልዕክተኛው መልቀቅ አሜሪካ በኢትዮጵያ የተረጋጋ ሰላም እንዲመጣ ለማደራደር የምታደርገውን ጥረት የሚያደናቅፍ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
አንጋፋው ዲፕሎማት ሳተርፊልድ ፤በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለመፍታት እና ጎረቤት ሱዳን ከአስርተ አመታት በኋላ ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ምላሽ ለመስጠት እና አሜሪካ የምታደርገውን ጥረት ለማስፈጸም የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ልዩ መልዕክተኛ ተደርገው በጥር ወር በፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን መሾማቸው የሚታወስ ነው።
ሳተርፊልድ የተሾሙት ከሳቸው በፊት የነበሩትን አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን ተክተው እንደነበርም አይዘነጋም።