ህወሓት “ኦባሳንጆ የሚያመቻቹት ነገር ፍትሀዊ ውጤት ይኖረዋል ብዬ አላምንም” አለ
ህወሃት፤ የአፍሪካ ሕብረት የመደባቸው ዲፕሎማት ለኢትዮጵያ መንግስት “ቅርብ ናቸው”ብሏል
ህወሃት፤ የአፍሪካ ሕብረት የመደባቸው ዲፕሎማት ለኢትዮጵያ መንግስት “ቅርብ ናቸው”ብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት እና ሕወሃትን ለማደራደር አዲስ አበባ እና መቀሌ ሲመላለሱ የቆዩት የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በህወሓት ትችት ቀረበባቸው፡፡
መንግስት በሽብር የፈረጀው ሕወሃት ቡድን ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ የምዕራባውያን ዲፕሎማቶች በመቀሌ ጉብኝት አድርገው ከተመለሱ በኋላ በክልሉ ሊገኙ መገኛኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሕግ የሚፈልጋቸው አቶ ጌታቸው ረዳ የአፍሪካ ሕብረት የቀንዱ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ለኢትዮጵያ መንግስት ቅርብ መሆናቸው ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ኦባሳንጆን ቡድናቸው በግል እንደማይጠላቸው ነገር ግን “ስድስቴ፤ ሰባቴ ስንቀበላቸው ምንም ያስቀመጡት ፍኖተ ካርታ የላቸውም” ሲሉም ነው አፍሪካ ሕብረትን ከፍተኛ ተወካዩ የተቹት።
ህወሓት፤ የአፍሪካ ህብረት ጠላት ነው ብሎ እንዳልፈረጀና የአፍሪካ ጉዳዮችን በአፍሪካ ይፈታሉ በሚለው አቋም ላይ ልዩነት እንደሌለው ገልጸዋል፡።
የኢትዮጵያ መንግስት ለ”ድርድር ፍቅር አለው፤ በድርድሩ ሰበብ ግዜ ለመግዛት የመጠቀም አካሄድ ግን እስከወዲያኛው መጠበቅ አንችልም” ሲሉም ነው አቶ ጌታው የተናገሩት።
የአፍሪካ ሕብረት የቀንዱ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ “መንግሰትን የሚሰሩትን ብታዩ እያሉ ያመሰግናሉ ስለዚህ ሁኔታቸው አላማረንም፤ እሳቸው የሚያመቻቹት ነገር ፍትሀዊ ውጤት ይኖረዋል ብለንም አናምንም” ብለዋል።
ምንም እንኳን ህወሃት ኦባሳንጆን ቢቃወምም አፍሪካ ሕብረት ግን ሚና ሊኖረው ይችላል ብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ፤ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ በመቀሌ ከተማ ከህወሀት ጋር የተገናኙ ዲፕሎማቶች በሰላም ንግግሩ ላይ ትኩረት አለማድረጋቸውን ገልጸው፤ መንግሥት ከህወሃት ጋር ያደርገዋል የተባለው ንግግር የሚመራው በአፍሪካ ሕብረት ብቻ እንደሆነ ትናንትና ገልጸዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ቀደም ብሎ በትዊተር ገጻቸው፤ መንግስት በሽብር ከፈረጀው ህወሓት ጋር በየትኛውም ቦታና ጊዜ መነጋገር እንደሚችል ገልጸው ነበር።
ህወሓት በበኩሉ የአፍሪካ ሕብረት ከኦባሳንጆ ይልቅ፤ ኡሁሩ ኬንያታን ወይም ታቦ ኢንቤኬን ወይም ሌላ ሰው ከሰየመ ችግር እንደሌለበት በቃል አቀባዩ በኩል ገልጿል።
“የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጦርነትን ስላላወገዘ ከዚህ ሰወዬ ፍትሕ አንጠብቅም አላልንም ይልቁንም ራሳቸው ኦባሳንጆ መስራት የሚገባቸውን ሳይሰሩ እየመጡ ስለሆነ ነው” ብለዋል አቶ ጌታቸው ረዳ።
የምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ወደ ትግራይ የተጓዙት ማክሰኞ ዕለት ሲሆን ፤ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ይካሄዳል ተብሎ የሚገመተውን ንግግር ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን በመግለጫቸው አስታውቀዋል።