ህወሃት ከመንግሥት ጋር ለመደራደር ኡሁሩ ኬንያታን መርጧል
የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የተጓዙ ዲፕሎማቶች ህወትን ሲለማመጡ እንደነበር ገለጸ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ወደ መቀሌ ተጉዘው ስለነበሩት አምባሳደሮች ገለጻ ሰጥተዋል።
ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትሩ ሬድዋን ሁሴን በመቀሌ ከተማ ከህወሀት ጋር የተገናኙ ዲፕሎማቶች በሰላም ንግግሩ ላይ ትኩረት አለማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ዲፕሎማቶች በመቀለ በነበራቸው ቆይታ መንግሥት ደስተኛ አለመሆኑን በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል።
አምባሳደር ሬድዋን፤ ወደ መቀሌ ተጉዘው የነበሩት ዲፕሎማቶች ለሰላም ንግግር ሂደቱ ጥረት ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ይህንን አለማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ወደ መቀሌ የተገዙት የአሜሪካ፤ የተመድ፤ የአውሮፓ ህብረት፣ የካናዳ የጣሊያን ዲፕሎማቶች ትኩረት አድርገው የነበረው ህወሃት ባስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ላይ መሆኑን ብሔራዊ የደህንነት አማካሪው ተናግረዋል።
በመሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ የመንግሥት አቋም ግልጽ እንደሆነ ያነሱት አምባሳደር ሬደዋን፤ አገልግሎት ለማስጀመር ግን የሰላም ንግግር መጀመር አለበት ብለዋል።
ዲፕሎማቶቹ ከመቀለ ጉዟ በኋላ "ያልተገደብ የሰብዓዊ እርዳታ " የሚል ጉዳይ ማንሳታቸው ትክክል እንዳልሆነ ይልቁንም አሁን ላይ ወደ ክልሉ ያልተገደብ በረራ እንዲሁም ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እየተጓዙ መሆኑን አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል።
አምባሳደር ሬደዋን፤ መንግስት ከህወሃት ጋር ያደርገዋል ተብሎ የሚገመተው ንግግር የሚመራው በአፍሪካ ሕብረት ብቻ መሆኑንም ገልጸዋል። የመንግስት አቋም የሰላም ንግግሩ በአዲስ አበባው ተቋም ብቻ እንዲካሄድ እንደሆነም ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።
መንግሥት ከህወሃት ጋር ያደርገዋል የተባለው ንግግር የሚመራው በአፍሪካ ሕብረት መሆን እንዳለበት ቀደም ሲል ገልጾ ነበር።
ህወሃት በበኩሉ ከመንግስት ጋር ለሚያደርገው ድርድር የኬንያን ፕሬዝዳንት ምርጫው እንደሚያደርግ ገልጿል።
የምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ወደ ትግራይ የተጓዙት ማክሰኞ ዕለት ሲሆን መንግሥት በሽብር ከፈረጀው ህወሓት እና በህግ ከሚፈልጋቸው አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
ዲፕሎማቶቹ፤ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ይካሄዳል ተብሎ የሚገመተውን ንግግር ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን በመግለጫቸው አስታውቀዋል።