አራት የአፍሪካ አገራት አሸባሪዎችን ለመውጋት ጦራቸውን ወደ ሞዛምቢክ ልከዋል
አሜሪካ አምስት አፍሪካዊያንን በሽብርተኝነት መዝገቧ ላይ አሰፈረች።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እንዳሉት አገራቸው አምስት ግለሰቦችን በሽብርተኝነት መዝገቧ ላይ አስፍራለች።
በሽብርተኝነት ላይ ስማቸው ከሰፈሩ ግለሰቦች መካከል የሞዛምቢኩ ቦኖሜድ ማቹድ ኦማር ዋነኛው ሲሆን ይህ ግለሰብ በሞዛምቢክ እና በታንዛኒያ በደረሱ የሽብር ጥቃቶች ጀርባ እጁ አለበት ተብሏል።
ይህ ግለሰብ በሞዛምቢክ የሚንቀሳቀሰው የእስላማዊ ቡድን ቅርንጫፍ ሲሆን በአገሪቱ በርካታ የሽብር ተግባራትን እንደፈጸመ ሮይተርስ ዘግቧል።
ሲዳንግ ሂታ እና ሳሌም አል ሀሰን የተባሉ ሁለት ግለሰቦች ደግሞ በማሊ የአልቃይዳ ቅርንጫፍ መሪዎች ሲሆኑ በአሜሪካ ዓለም አቀፉ የሽብርተኞች መዝገብ ላይ ስማቸው የሰፈሩ ሰዎች ናቸው።
በሶማሊያ የአልሻባብ መሪ መሆናቸው የተገለጸው አሊ መሀመድ ሬግ እና አብዲከድር መሀመድ ደግሞ በተጨማሪነት በአሜሪካ የሽብር መዝገብ ላይ ስማቸው የሰፈሩ ግለሰቦች መሆናቸው ተጠቅሷል።
እነዚህ ግለሰቦች በአሜሪካ እና በሌሎች አገራት ያላቸው ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ እና እንዳይገበያዩ እገዳ ተጥሎባቸዋል ተብሏል።
በሞዛምቢክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ንጹሀን ዜጎችን ኢላማ ያደረጉ በርካታ የሽብር ወንጀሎች በመፈጸም ላይ ሲሆኑ አደጋውን ለመቀልበስ የጎረቤት አገራት ሰላም አስከባሪ ጦር አዋጥተው መሰማራት ጀምረዋል።
ሩዋንዳ፤ቦትስዋና፤አንጎላ እና ደቡብ አፍሪካ የሞዛምቢክ መከላከያ ጦር በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ከሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር እያደረገ ያለውን ውጊያ ለማገዝ ጦራቸውን ያዋጡ አገራት ናቸው።