ምኑቺን ከአል ቡርሃን እና ከሀምዶክ ጋር በሕዳሴ ግድብ እና በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ይወያያሉ
በግብፅና ሱዳን ጉብኝት ለማድረግ ወደ አፍሪካ የገቡት የአሜሪካው የግምጃ ቤት ኃላፊ ስቴቨን ምኑቺን ካርቱም መግባታቸውን የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
ስቴቨን ምኑቺን ካርቱም ሲደርሱ በሱዳን የገንዘበና ኢኮኖሚ ዕቅድ ሚኒስትር ዶ/ር ሂባ መሐመድ አሊ እና በሱዳን የአሜሪካ አምባሳደር አቀባበል እንደተረገላቸው ተገልጿል፡፡ ትናንት ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር በካይሮ የተወያዩት ምኑቺን በካርቱም ቆይታቸው ከሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ መንበር አብዱል ፋታህ አል ቡርሃን እና ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ (ዶ/ር ) ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
ምኑቺን ትናንት በግብፅ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየሰራችው ባለው የሕዳሴ ግድብ ሰሞነኛ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት መግለጹ ይታወሳል፡፡
ምኑቺን በሱዳን ቆይታቸውም እንዲሁ በግብፅ እንዳደረጉት ሁሉ ስለ ሕዳሴ ግድብ ድርድርና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ውይይት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡
ስቴቨን ምኑቺን የሕዳሴ ግድብ ድርድር በአሜሪካ ሲደረግ ፣ ከታዛቢነት ሚናቸው አልፈው ፣ ድርድሩን በሦስተኛ ወገንነት ሲመሩ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ በአሜሪካ ግምጃ ቤት የተዘጋጀውን ሰነድም ኢትዮጵያ እና ሱዳን አንፈርምም ማለታቸው ይታወሳል፡፡