መሀመድ ቢን ዛይድ ለፍልስጤም የ20 ሚሊየን ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግ አዘዙ
ፕሬዝዳንቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን በፍጥነት መድረስ ይገባል ብለዋል
ኤምሬትስ ሃማስ እና እስራኤል ግጭት አቁመው ወደ ንግግር እንዲመለሱ ጠይቃለች
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ለፍልስጤም በአስቸኳይ 20 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንዲደረግ አዘዙ።
ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ቅዳሜ በጀመረው የሃማስ እና እስራኤል ግጭት ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን መድረስ እንደሚገባ መናገራቸውን የሀገሪቱ ዜና አገልግሎት ዋም ዘግቧል።
ድጋፉ ለፍልስጤም ስደተኞች አስቸኳይ ድጋፍ በሚያቀርበው የመንግስታቱ ድርጅት ኤጀንሲ በኩል ይቀርባል ተብሏል።
በሃማስ እና እስራኤል መካከል አራተኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት ከ1 ሺህ 750 በላይ ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል።
እስራኤል በጋዛ በቀጠለችው ድብደባም የሚያልፈው የሰው ህይወት እና የመኖሪያ ቀያውን ጥሎ የሚሸሸው እየተበራከተ ሄዷል።
የመንግስታቱ ድርጅትም በጋዛ ፈጣን ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች አለማቀፉ ማህበረሰብ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ከጠየቀ ዋል አደር ብሏል።
የሃማስ እና እስራኤል ግጭት እንዲቆምና ሁለቱም ወገኖች ወደ ንግግር እንዲመለሱ የጠየቀችው ኤምሬትስ ፈጣን የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ በመወሰን ቀዳሚ ሆናለች።
አቡዳቢ ሁለቱም ወገኖች ንጹሃንን ኢላማ ከሚያደርጉ ጥቃቶች እንዲታቀቡ አሳስባለች።
ግጭቱ የፍልስጤም እና እስራኤልን የአመታት ውጥረት ለማርገብ የሚደረጉ ቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን ያስቆማል በሚልም ተቃውሞዋን ማሰማቷ ይታወሳል።