አረብ ኢምሬት ከአፍሪካ ወጪና ገቢ ባንክ 100 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ ገዛች
የሀገሪቱ ቦንድ ግዢው የአፍሪካን ዘላቂ ኢንቨስትመንት ለማነቃቃት ያግዛል ተብሏል
28ኛው የተመድ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በዱባይ እየተካሄደ ይገኛል
አረብ ኢምሬት ከአፍሪካ ወጪና ገቢ ባንክ 100 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ ገዛች።
በአረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የኮፕ28 አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የዓለም ሀገራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎችን እና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ጋር በመምከር ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ ጉባኤ አካል ጎን ለጎንም የአቡዳቢ ኢንቨስትመንት ባለስልጣን በአፍሪካ ዘላቂ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በሚል የ 100 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ መግዛቱን አስታውቋል።
ባለስልጣኑ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ መጠን ያለው ቦንድ የገዛ ሲሆን በድጋሚ ከአፍሪካ ገቢና ወጪ ባንክ ቦንድ መግዛቱ ተገልጿል።
የቦንድ ግዢው የአፍሪካ ኤግዚም ባንክ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዳያጋጥመው ያደርጋል ተብሏል።
የዱባይ ኢንቨስትመንት ባለስልጣን ቦንድ ግዢ የአረንጓዴ ልማት ቦንድ ላይ ትኩረቱን አድርጓል የተባለ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶችን ለመቀነስ እንደሚያግዝም ተገልጿል።
ለ25 ዓመት ይቆያል የተባለው ይህ የቦንድ ግዢ ዓለም አቀፍ ተቋማት ትኩረታቸውን በአፍሪካ እንዲያደርጉ ይጠቅማልም ተብሏል።
የማይክሮሶፍት ኩባንያ መስራች እና ባለቤት የሆኑት ቢል ጌትን ጨምሮ በርካታ የቢዝነስ ሰዎች በኮፕ28 ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ የቢዝነስ ተቋማት መሪዎች በትናንትናው ዕለት ባደረጉት ውይይት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትን ለመከላከል አምስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያዋጡ አስታውቀዋል፡፡