በ55 ቀናት 129 አውሮፕላን - ከኤምሬትስ ወደ ጋዛ
አረብ ኤምሬትስ ለፍልስጤማውያን ከ9 ሺህ 290 ቶን በላይ አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ወደ ጋዝ ልካለች
አቡዳቢ በጋዛ ድጋፍ እንዲገባ ለጸጥታው ምክርቤት ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ መጽደቁ ይታወሳል
አረብ ኤምሬትስ በከባድ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ለሚገኙት ፍልስጤማውያን አስቸኳይ ድጋፍ ማቅረቧን ቀጥላለች።
የእስራኤልና ሃማስ ጥቃት ከተጀመረ አንስቶ ጦርነቱ እንዲቆም ስትወተውት የቆየችው አቡዳቢ፥ ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ንጹሃንን ለመጠበቅና አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው።
በ55 ቀናት ውስጥም በ129 አውሮፕላኖች የተጫኑ ድጋፎችን ወደ ግብጽ በመላክ በተሽከርካሪዎች ወደ ጋዝ እንዲገቡ አድርጋለች።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በሚመሩት “ጋላንት ናይት 3” በተሰኘው ዘመቻ እስካሁን 9 ሺህ 296 ቶን ስብአዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ ተልኳል።
ከኤምሬትስ የተላኩ ድጋፎችን የጫኑ 121 ተሽከርካሪዎች ከግብጽ ወደ ጋዛ የገቡ ሲሆን፥ በቀጣይም ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኤምሬትስ በውሃ ጥም ለሚሰቃዩ ፍልስጤማውያን በቀን ከ2 ሚሊየን ሊትር በላይ ውሃ ማቅረብ የሚችሉ ሶስት የውሃ ማውጫ ማሽኖችን መትከሏንም የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ አስፍሯል።
ሀገሪቱ በጋዛ 150 አልጋዎች ያሉት ፊልድ ሆስፒታል በመክፈትም በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ፍልስጤማውያን ቀዶ ጥገናን ጨምሮ የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት አባሏ አረብ ኤምሬትስ በጋዛ እርዳታ እንዲገባ ለምክርቤቱ ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ በቅርቡ መጽደቁ ይታወሳል።