አረብ ኤሚሬት ለኢትዮጵያ የሚሆን የ85 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ይፋ አደረገች
ኤሚሬት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን እንደምታደርግም ነው ያስታወቀችው
ድጋፉ ለአንገብጋቢ ሰብዓዊ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት የሚውል ነው ተብሏል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ለኢትዮጵያ የሚሆን የ85 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ይፋ አደረገች፡፡ ድጋፉ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታዎች አስተባባሪ ተቋማት በኩል ለተጠቃሚዎች የሚደርስ ነው ተብሏል፡፡
ከዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ ከዓለም የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማህበራት፣ ከዩኒሴፍ እና ሌሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ተቋማት ጋር እንደሚሰራም ነው የተገለጸው፡፡
ዩኤኢ ድጋን እንደምታደርግ ያስታወቀችው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታዋ ሼክ ሻክቦት ቢን ናህያን አል ናህያን፣ የተመድ የሰብዓዊ እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ እንዲሁም በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በተገኙበት በተካሄደ የበይነ መረብ ስብሰባ ነው፡፡
ግሪፊትስ ለድጋፉ ዩኤኢን አመስግነዋል፡፡ አምባሳደር ታዬ ስለ ድጋፉ ያሉት ነገር እንዳለ አላስታወቁም፡፡
ሼክ ሻክቦት በበኩላቸው ሃገራቸው በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ ገልጸዋል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በቀንዱ አካባቢ ያለውን የከፋ ሰብዓዊ ሁኔታ ይበልጥ ማባባሱን በማስታወስም የዛሬው ድጋፍ የሰብዓዊ ተቋማትን አቅምና ተደራሽነት ለማሳደግ እንደሚያስችልም ተናግረዋል፤ በቀጣናው አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታዎች እንደሚያስፈልጉ በመጠቆም፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የከፋ የተባለ ድርቅን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡ 12 ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን ለድርቁ ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡ የእንስሳት ሃብታቸውን ጨምሮ ብዙ ነገራቸውን ያጡም ጥቂት አይደሉም፡፡
ይህ ጦርነቱን ተከትሎ በከፋ ሰብዓዊ ድቀት ውስጥ በምትገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋል እውነታም ነው፡፡ በሱማሌ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ብቻ ከ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎች በድርቁ ምክንያት ችግር ላይ መውደቃቸውን አል ዐይን መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የዛሬው ድጋፍ መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡ ኤሚሬት በሶማሊያ ለድርቁ ሰለባዎች የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎችን እንደምታደርገም አስታውቃለች፡፡ ከሰሞኑ 35 ቶን የምግብ እርዳታ ለትግራይ ክልል መላኳን ማስታወቋም የሚታወስ ነው፡፡