አረብ ኢምሬትስ በወንጀል የሚጠረጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን ቱጃሮች በቁጥጥር ስር አዋለች
አቱል እና ራጄሽ ጉፕታ ከቀድሞ ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማ ጋር ተመሳጥረው ሀብት አካብተዋል በሚል በህግ ሲፈለጉ የቆዩ ናቸው
የጉፕታ ቤተሰብና ዙማ በጣም ከመቀራረባቸው የተነሳ "ዙፕታ" የተሰኘ ቅጥል ስም ወጥቶለቸው ነበር
በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ የስልጣን ዘመን በፖለቲካዊ ሙስና ተከሰው የነበሩት ወንዳማማቹ ቱጃሮች ራጄሽ ጉፕታ እና አቱል ጉፕታ አረብ ኢምሬትስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ደቡብ አፍሪካ አስታወቀች፡፡
አቱል እና ራጄሽ ጉፕታ ከቀድሞው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማ ጋር ተመሳጥረው ሀብት አካብተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው በህግ ሲፈለጉ የነበሩ ነው፡፡
ወንድማማቾቹ በፈረንጆቹ ከ2009 እስከ 2018 በስልጣን ላይ ከነበሩት ዙማ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ተጠቅመው ኮንትራት በመጨረስ፣ የመንግስትን ሀብት አላግባብ በመበዝበዝ፣በካቢኔ ሹመት ላይ ተጽእኖ በማሳደር እና የመንግስትን ገንዘብ በማጭበርበር ወንጀል ተከሰዋል።
የጉፕታ ቤተሰብና ዙማ በጣም ከመቀራረባቸው የተነሳ "ዙፕታ" የተሰኘ ቅጥል ስም ተበጅቶላቸው እንደነበርም ነው የሚነገረው።
ከዙማ ሚስቶች መካከል አንዷ እንዲሁም ወንድና ሴት ልጆቻቸው በጉፕታ ቤተሰብ ኩባንያዎች ውስጥ ትላልቅ ቦታ ይዘው ይሰሩ እንደነበርም ጭምር ይነሳል።
“ባለስልጣናት ከጉፕታ ቤተሰብ ቀጥታ ትዕዛዝ መጥቶ ውሳኔ እንድንሰጥ ተገደን እናውቃለን ሲሉ በይፋ ተናግረው ያውቃሉ”ም ይላል የሮይተርስ ዘገባ።
የገንዘብ ሚኒስቴርና የደቡብ አፍሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኤስኤቢሲን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካ ኤርዌይስ እንዲሁም የባቡር ትራንስፖርት ከጉፕታ ቤተሰብ ጋር ተያይዞ ስማቸው ከሚነሳ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
የደቡብ አፍሪካው ጉምቱ ዳኛ አራት ዓመት የፈጀውን ምርመራ ውጤት ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ የጉፕታ ቤተሰብ ገዥው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲን ሲዘውሩ ነበር ማላታቸውም የሚታወቅ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ዙማ እና የጉፕታ ቤተሰብ ምንም አይነት ጥፋት እንዳልፈጸሙ ክሱን ውድቅ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ዙማ ባለፈው ዓመት የጉፕታ ቤተሰብ ላይ “አልመሰክርም ” በማለታቸው ብቻ ለ15 ወራት እስራት መዳረጋቸው የዚሁ ማሳያ ነው፡፡
በፈረንጆቹ በ2018 ዙማ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ የህንድ ዝርያ ያላቸው ወንድማማቾች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ወጥተዋል።
ይህን ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ መንግስት፤ በዙማ የስልጣን ዘመን የተፈጸሙ የስርቆት ውንጀላዎችን ለመመርመር በ2018 የፍትህ ኮሚሽን ማቋቋሙ አይዘነጋም።
ጉዳዩ ሲንከባለል ቆይቶ አሁን ላይ የወንድማማቹ ቱጃሮች በቁጥጥር ስር መዋል፤ ተጠያቂነት ሊያስከትል የሚችል ጥሩ አጋጣሚ ነው ተብለዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት እንደሚሉት ሀገሪቱ ባላቸው “እስረኛን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት” መሰረት ወንድማማቾቹን ለማምጣት ከዩኤኢ ጋር መምከር ጀምራለች።
የደቡብ አፍሪካ የፍትህ እና ማረሚያ አገልግሎት ሚኒስቴር በሰጠው አጭር መግለጫ "በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ የተለያዩ የህግ አስከባሪ ኤጀንሲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት ቀጣይ ነው" ሲል ተናግሯል፡፡
በዚህም የተደረሰው ስምምነት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ መንግስት በጉፕታ ቤተሰብ ክስ ለመመስረት ያስችላቸዋል ተብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የደቡብ አፍሪካ ትልቁ ተቃዋሚ ፓርቲ ዴሞክራቲክ አልያንስ እስሩን በደስታ ተቀብሏል።
ፓርቲው ባወጣው መግለጫ "ይህ በእውነትም ሀገራችንን በውስጥም ሆነ በውጭ ሆነው ለዓመታት የዘረፉትን እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን ዛሬ ለገጠማት ችግር በቀጥታ ተጠያቂ የማድረግ የመጀመሪያ እርምጃ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብሏል፡፡
አቱልና ራጄሽ ጉፕታ ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጡት ከአፓርታይድ መውደቅ በኋላ በፈረንጆቹ 1993 ነበር።በኮምፒውተር ንግድ የጀመረው ስራቸው ተጧጡፎ ፤ በደቡብ አፍሪካ ከሚጠቀሱ ቱጃር ቤተሰቦች አንዱ እስከመሆን የደረሱም ናቸው፡፡