40 ዓመት ያስቆጠረው የአረብ ኢምሬትስ - ቻይና ግንኙነት
የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከቻይና ጋር በ1984 ነበር ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የመሰረተችው
ቻይና በመካከለኛው ምስራቅ ካሉ ሀገራት ጋር ካላት የንግድ ልውውጥ አረብ ኢምሬትስ የመጀመሪያዋ ሀገር ናት
የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከቻይና ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 40ኛ ዓመት እየተከበረ ይገኛል።
የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት 40ኛ ዓመት ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ይከበራል ተብሏል።
በጎርጎሮሲያዊያን ዘመን አቆጣጠር ሕዳር 1984 የተጀመረው የቻይና እና አረብ ኢምሬት ወዳጅነት አሁን ላይ ግማሽ ክፍለ ዘምን ሊሞላው 10 ዓመታት ብቻ ይቀረዋል።
አረብ ኢምሬትስ በቻይና ኢምባሲዋን ከከፈየች በኋላ የመጀመሪያውን ሁነት በኪንግዳኦ ያዘጋጀች ሲሆን ለ40ኛ ዓመት በዓልም እየተከበረባት ይገኛል።
የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ሲሆን ከነዳጅ ውጪ ያለው የንግድ ልውውጥ ከ800 ጊዜ በላይ ጭማሪ አሳይቷል።
ኢምሬትስ የቻይና ዋነኛ የንግድ አጋር ስትሆን ቤጂንግ 60 በመቶ ምርቶቿን ከአረብ ኢምሬት ወደ ሌሎች ሀገራት እየላከች ትገኛለች።
ቱሪዝም ሌላኛው የሁለቱ ሀገራት ዋነኛ የተሳሰሩበት ጉዳይ ሲሆን ባለፉት 10 ወራት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቻይናዊያን አረብ ኢምሬትን ጎብኝተዋል ተብሏል።
ሌላኛው የቻይና-አረብ ኢምሬት የዲፕሎማሲ ስራ ትምህርት እና ባህል ሲሆን ከዚህ አንጻር አረብ ኢምሬት ቻይንኛ ቋንቋ ከአረብኛ እና እንግሊዘኛ በመቀጠል ሶስተኛው የስራ እና ትምህርት ቋንቋዋ አድርጋለች።
171 የአረብ ኢምሬትስ ትምህርት ቤቶች ቻይንኛ ቋንቋን በማስተማር ላይ ሲሆኑ ይህም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ያጠናክረዋል።