የእስራኤል ካቢኔ ከዩኤኢ ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አጸደቀ
የዩኤኢው መሐመድ ቢን ዛይድ በቅርቡ በእስራኤል ጉብኝት እንደሚያደርጉ ቤኒያሚን ኔታንያሁ ገልጸዋል
ለእስራኤልን-ፍልስጤም ግጭት ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሰጥ ካቢኔው ባጸደቀው ረቂቅ ላይ ተገልጿል
የእስራኤል ካቢኔ ከዩኤኢ ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አጸደቀ
በቅርቡ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጋር ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመረችው እስራኤል ቀደም ሲል ከአቡዳቢ ጋር ያደረገችውን ስምምነት የሀገሪቱ ካቢኔ ዛሬ አጽድቆታል፡፡
ካቢኔው ያጸደቀው ረቂቅ “በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና በእስራኤል መንግስት መካከል የሰላም ስምምነት ፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እና ሙሉ መደበኛነት” በሚል ርዕስ ለፓርላማው ይቀርባል ተብሏል፡፡
የሁለቱን ህዝቦች ትክክለኛ ፍላጎቶች እና ምኞቶች በሚያሟላ መንገድ “ለእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት ፍትሃዊ ፣ ሁሉን አቀፍ ፣ ተጨባጭ እና ዘላቂ መፍትሄን ለማሳካት” እና ሁለገብ የመካከለኛው ምስራቅ ሰላምን ፣ መረጋጋትን እና ብልጽግናን ለማምጣት በረቂቁ ቃል ተገብቷል፡፡
ፓርላማው የቀረበውን ሀሳብ ይቃወማል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የአቡዳቢውን አልጋ ወራሽና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጦር ምክትል ጠቅላይ አዛዥ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያንን ማናገራቸውንና በቅርቡ ለመገናኘት መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያን እና ቤኒያሚን ኔታንያሁ
በዚህ ሳምንት ከመሐመድ ቢን ዛይድ ጋር መነጋገራቸውን የገለጹት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ልዑል አልጋወራሹ ወደ እስራኤል መጥተው ጉብኝት እንዲያደርጉ መጋበዛቸውንና እርሳቸውም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን እንዲጎበኙ ጥሪ እንደቀረበላቸው አስታውቀዋል፡፡ በቅድሚያ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ልዑክ ወደ እስራኤል እንደሚያቀናና በኋላም የእስራኤል ልዑክም አቡዳቢን እንደሚጎበኝ አስታውቀዋል፡፡
ዩኤኢ እና እስራኤል ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመጀመር የሚያስችል የሰላም ስምምነት ያደረጉት ቴላቪቭ እና አቡዳቢ የተፈጥሮ ጋዝን ወደ አውሮፓ መላክን ጨምሮ በመልካም ትብብርና የኢንቨስትመንት ጉዳይ ላይ መወያየታቸው ይታወሳል፡፡ ሁለቱ ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል እና የተፈጥሮ ጋዝ ወደ አውሮፓ የሚያጓጉዙበትን መስመር በመዘርጋት ለገበያ ማቅረብ በሚችሉበት ጉዳይ ላይ መነጋገራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
እስራኤልና ዩኤኢ እ.ኤ.አ. ባለፈው መስከረም 15 ነው የሰላም ስምምነት የተፈራረሙት፡፡