የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግስት የግብይት ማእከላት ለ 2 ሳምንታት እንዲዘጉ ወሰነ
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግስት የግብይት ማእከላት ለ 2 ሳምንታት እንዲዘጉ ወሰነ
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግስት በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የገበያ ማእከላት እና ሞሎች የአሳ፣ የስጋና የአትክልት ገበያዎችን ጨምሮ ለሁለት ሳምንታት እንዲዘጉ ወስኗል፡፡
ውሳኔው ሊታደስ እንደሚችልም ነው የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር እና ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜና የአደጋ መከላከል ቁጥጥር ባለስልጣን ባወጡት መግለጫ ያስታወቁት፡፡
ውሳኔው ከ 48 ሰዓታት በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን እና ክትትል እንደሚደረግበትም በመግለጫው ተገልጿል፡፡
በዱባይ ሞል በርካታ ሰዎች ለግብይት ሲንቀሳቀሱ
መድኃኒት ቤቶች፣ የምግብ እና መጠጥ መደብሮች በሚዘጉ የግብይት ማእከላት ውስጥ አይካተቱም፡፡ ሬስቶራንቶች ደንበኞችን ተቀብለው ማስተናገድ ባይችሉም ገዝተው ወደቤታቸው ለሚወስዱ ተጠቃሚዎች ግን አገልግሎት መስጠታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
መንግስት የሀገሪቱ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡም አግዷል
እንደ ምግብ እና መድኃኒት ላሉ እጅግ አስፈላጊ ጉዳዮች ወይም አንገብጋቢ ተግባራት ለመከወን ካልሆነ በስተቀር ህዝቡ ከቤቱ እንዳይወጣ የሀገሪቱ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግስት ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡
የሀገሩስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜና የአደጋ መከላከል ቁጥጥር ባለስልጣን በጋራ በሰጡት መግለጫ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዜጎች፣ ሌሎች ነዋሪዎች እና ጎብኚዎች በሀገሪቱ የጤናና የደህንነት ባለስልጣናት የሚወጡ መመሪያዎችን እንዲተገብሩ አሳስበዋል፡፡
የሀገሪቱ ነዋሪዎች ከቤት ለመውጣት በሚገደዱበት ጊዜም ቢሆን ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ንክኪ ከማድረግ እንዲቆጠቡ መንግስት ጥሪ አቅርቧል፡፡ በአንድ የቤት መኪና ውስጥ ከ 3 ሰው በላይ መንቀሳቀስ እንደሌለበትም በውሳኔው ተደንግጓል፡፡
ማንም የሀገሪቱ ነዋሪ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ካላስፈለገው በስተቀር ወደ ሆስፒታሎች መሄድ እንደሌለበትም ተገልጿል፡፡
በመንግስት የተላለፈውን ውሳኔ ጥሰው የሚገኙ ሰዎች በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የተላላፊ በሽታዎች ህግ መሰረት እንደሚቀጣም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
ከረቡእ መጋቢት 16/2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሀገሪቱም ይሁን ከሀገሪቱ ውጭ የሚደረጉ በረራዎች እንደሚቋረጡም የሀገሪቱ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከ150 በላይ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ይገኙባታል፡፡