እንግሊዝ አንድን ሰው በጥፊ መቷል ያለችውን የፓርላማ አባል ከስራ አገደች
የፓርላማ አባሉ መንገድ ዳር ሰውን ሲደበድብ የሚሳይ ምስል በስፋት ተሰራጭ ታይቷል
የሀገሪቱ ፖሊስ የፓርላማ አባሉ ለምን ሰው እንደመቱ ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል
እንግሊዝ አንድን ሰው በጥፊ መቷል ያለችውን የፓርላማ አባል ከስራ አገደች፡፡
ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ በተካሄደ የብሪታንያ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ማግኘቱን ተከትሎ ስልጣን የያዘው ሰራተኞች ፓርቲ የምክር ቤት አባሉን አግዷል፡፡
ፓርቲው የህግ አውጪ ምክር ቤት አባሉን ከስራ ያገደው ግለሰቡ አንድን ሰው በጥፊ ሲመቱ የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ ትስስርገጾች ላይ በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ ነው፡፡
ከምክር ቤት አባልነቱ በጊዜያዊነት የታገደው ማይክ አሜስበሪ የ55 ዓመት እድሜ ያለው ሲሆን ለምን ሌላ ሰው በጥፊ እንደመታ አልታወቀም፡፡
የሰራተኞች ፓርቲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ማይክ ጉዳዩን እየመረመረ ካለው የቸሻየር ፖሊስ ጋር በጋራ እየሰሩ ናቸው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ምርመራው ተረጋግጦ ማይክ አሜስበሪ ወንጀል አለመፈጸማቸው እስከሚረጋገጥ ድረስም ከህግ አውጪ ምክር ቤት አባልነት እንደታገዱ ፓርቲያቸው አስታውቋል፡፡
የሰራተኞች ፓርቲ ተቀናቃኝ የሆኑት ሪፎርም ዩኬ እና ወግ አጥባቂ ፓረቲዎች የምክር ቤት አባሉ የፈጸሙት ነገር በፖሊስ እየተመረመረ መሆኑ መልካም ነገር ነው ብለዋል፡፡
የምክር ቤት አባሉ ራሳቸውን ከሀላፊነት እንዲያገሉ እየተጠየቁ ሲሆን ማይክ አሜስበሪ እስካሁን ፖሊስን እየተባበሩ ከመሆናቸው ውጪ ተጨማሪ ነገር ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
ማይክ አሜስበሪ ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ በቸሻየር የህግ አውጪ ፓርቲ አባል ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ከ2018 እስከ ያዝነው 2024 ዓመት ድረስም የትይዩ ሚኒስትር ናቸው፡፡