ኤምሬትስ እና ግብጽ በጋዛ ለዘጠነኛ ጊዜ ከአየር ላይ ድጋፎችን አደረሱ
የሀገራቱ ሁለት አውሮፕላኖች በዛሬው እለት ከ33 ቶን በላይ የሚመዝኑ ምግብና ሌሎች ድጋፎችን በፓራሹት ወርውረዋል
ኤምሬትስ ለፍልስጤማውያን በ213 አውሮፕላኖች፣ 946 ተሽከርካሪዎችና ሁለት መርከቦች ሰብአዊ ድጋፎችን ልካለች
አረብ ኤምሬትስ እና ግብጽ በጋዛ ለዘጠነኛ ጊዜ ከአየር ላይ ድጋፎችን አደረሱ።
በዛሬው እለት የሀገራቱ ሁለት አውሮፕላኖች 33 ቶን የሚመዝኑ ምግቦችና ሌሎች ሰብአዊ ድጋፎችን በፓራሹት በመወርወር ተደራሽ አድርገዋል።
ይህም ከአውሮፕላኖች ላይ የተወረወረውን ሰብአዊ ድጋፍ 405 ቶን ማድረሱ ነው የተገለጸው።
ኤምሬትስ በእስራኤል የአየርና ምድር ጦር ድብደባ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን ለመድረስ “ጋላንት ናይት 3” የተሰኘና በፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ የሚመራ ዘመቻ መጀመሯ ይታወሳል።
“የበጎነት ወፎች” የሚል ስያሜ የሰጠችው ከአውሮፕላኖች ላይ ድጋፎችን በፓራሹት የመወርወር ዘመቻም በኤምሬትስ በጎአድራጊ ተቋማትና የሀገሪቱ ቀይ መስቀል ማህበር እየታገዘ ምግብና ህይወትን ለማስቀጠል ወሳኝ የሆኑ ግብአቶችን በማድረስ ላይ ይገኛል።
የኤምሬትስ አየር ሃይል አውሮፕላኖች ከግብጽ አቻቸው ጋር በመተባበር ሲያደርሱት የቆዩት ድጋፍ እንደሚቀጥልም የኤምሬትስ መንግስት ገልጿል።
አቡ ዳቢ የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በ213 አውሮፕላኖች፣ 946 ተሽከርካሪዎች እና ሁለት መርከቦች ሰብአዊ ድጋፎችን በመላክ ለፍልስጤማውያን የቁርጥ ቀን ደራሽነቷን አሳይታለች።
ከ21 ሺህ ቶን በላይ እንደ ምግብ፣ መድሃኒት እና ሌሎች አስቸኳይ ድጋፎችን ማድረሷም ይታወሳል።
ኤምሬትስ በጋዛ ስድስት የውሃ መሳቢያዎችን በመትከልም በቀን ከ3 ሚሊየን ሊትር በላይ ውሃ በማመንጨት ከ600 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ተጠቃሚ ማድረጓ አይዘነጋም።
በደቡባዊ ጋዛ የገነባችው ተንቀሳቃሽ (ፊልድ) ሆስፒታልም በጦርነቱ ለተጎዱ ፍልስጤማውያን ፈጣን የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ከ85 በመቶ በላይ ፍልስጤማውያንን ከቀያቸው ያፈናቀለውና ከ60 በመቶ በላይ የሰርጡን መሰረተ ልማት ያፈራረሰው ጦርነት እንዲቆምም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን ቀጥላለች።