በጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ በባህር ለማስገባት ታግዛለች የተባለችው የአሜሪካ መርከብ ጉዞ ጀምረች
መርከቧ በጋዛ ጊዜያዊ የባህር ወደብ ለመገንባት የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን መጫኗ ተገልጿል
በቆጽሮስ ወደብ 200 ሜትሪክ ቶን የምግብ እርዳታ ጭና የቆመችው መርከብ ዛሬ ወደ ጋዛ ጉዞ እንደምትጀምር ይጠበቃል
የአሜሪካ ወታደራዊ መርከብ ወደ መካከለኛ ምስራቅ ጉዞ ጀመረች።
ከቨርጅኒያ የጦር ጣቢያ የተነሳችውና “ጀነራል ፍራንክ ኤስ ቤንሰን” የሚል መጠሪያ ያላት መርከብ ለፍልስጤማውያን በባህር ድጋፍ እንዲደርስ ታግዛለች ተብሏል።
መርከቧ ወደብ በሌላት ጋዛ ከባህር ዳርቻዋ ጋር የተገናኘ “ጊዜያዊ የባህር ወደብ” ለመገንባት የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን የጫነች ስለመሆኗም ነው የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ (ሴንትኮም) ያስታወቀው።
አሜሪካ በጋዛ እገነባዋለው ያለችው ጊዜያዊ የባህር ወደብ በሁለት ወራት ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችልና 1 ሺህ አሜሪካውያን በግንባታው እንደሚሳተፉ ፔንታጎን ይፋ አድርጓል።
ውሳኔው አሜሪካ በየብስ እና በአየር የሚደረገው ድጋፍ አስቸጋሪ እና አደገኛ መሆኑን መረዳቷን ያመላክታል ተብሏል።
የአለምአቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ግን ፍልስጤማውያን አሁን ባሉበት ሰቆቃ 60 ቀናትን መጠባበቅ የሚችሉ አይደሉም እያሉ ነው።
የመንግስታቱ ድርጅትም ከ576 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን (ሩብ የጋዛ ህዝብ) በከባድ የምግብ እጥረት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን በመጥቀስ ሰብአዊ ድጋፍ በፍጥነት እንዲገባ ማሳሳቡ አይዘነጋም።
የአለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች የጦርነቱ አለመብረድና የእርዳታ ስርቆትን በምክንያትነት በመጥቀስ ድጋፋቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
በተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ደጋፍ እንዳይገባ መከልከሏ ያስወቀሳት እስራኤል፥ እርዳታ ለመቀበል የተሰባሰቡ ከ100 በላይ ፍልስጤማውያንን መግደሏ መገለጹም ይታወሳል።
ይህም አጋሯን አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራትና አለማቀፍ ተቋማትን ያስቆጣ እንደነበር የጠቀሰው ሬውተርስ፥ በጋዛ ከአውሮፕላን የሚወረወርም ሆነ በመኪና የሚገባ ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ ታምኗል ብሏል።
200 ሜትሪክ ቶን የምግብ እርዳታ ጭና በቆጵሮስ ላናርካ ወደብ የምትገኘው “አፕን አርምስ” መርከብ ዛሬ ወደ ጋዛ ጉዞ እንደምትጀምር መገለጹም ተስፋ ሰጪ ሆኗል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለጋዛ ቅርብ ከሆነችው ቆጽሮስ የሚነሳው አዲሱ የባህር መተላለፊያ ኮሪደር በጋዛ ፈጣን የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ እንደሚያስችል መግለጹ ይታወሳል።
የስፔን ምግባረሰናይ ድርጅት ንብረት የሆነችው መርከብ ጭነት የት እንደሚራገፍ፣ በእስራኤል ፍተሻ ይደረግበታል ወይ የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ግን እስካሁን አልተመለሱም።