ኤምሬትስ ለጋዛ 10 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የህክምና ግብአቶችን ለመለገስ ቃል ገባች
ሀገሪቱ ፈጣን የህምክና እገዛ ለሚፈልጉ ፍልስጤማውያን ለመድረስም በዳቮስ ከአለም ጤና ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራርማለች
ኤምሬትስ በጋዛ የፊልድ ሆስፒታል በመክፈት አገልግሎት እየሰጠች መሆኑ ይታወቃል
አረብ ኤምሬትስ በጋዛው ጦርነት ምክንያት ክፉኛ የተጎዳውን የጤና ስርአት ለመደገፍ የ10 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም ናቸው የ37 ሚሊየን ድርሃም (10 ሚሊየን ዶላር) ድጋፉን ይፋ ያደረጉት።
ድጋፉ መሰረታዊ የህክምና ቁሳቁሶችን ለማቅረብና በተለይ በአሳሳቢ የጤና ችግር ውስጥ ለሚገኙ ህጻናት በፍጥነት ለመድረስ ያስችላልም ተብሏል።
10 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡት የህክምና ቁሳቁሶች በሼክ ሞሃመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም አለማቀፍ ኢኒሼቲቭ በኩል ይቀርባሉ መባሉንም የኤምሬትስ የዜና ወኪል ዋም ዘግቧል።
የኢኒሼቲቩ ዋና ጸሃፊ ሞሀመድ አል ገርጋዊ በስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ከሚገኘው የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ከአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ድጋፉን የተመለከተ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ዶክተር ቴድሮስ በዚሁ ወቅት “በጋዛ በርካታ የጤና ተቋማት ተጎድተው የህክምና ግብአቶች እጥረት በስፋት በተከሰተበት በዚህ ወቅት ከኤምሬትስ የተገኘው ድጋፍ ወሳኝ ነው” ብለዋል።
የእስራኤልና ሃማስ ጥቃት ከተጀመረ አንስቶ ጦርነቱ እንዲቆም ስትወተውት የቆየችው አቡዳቢ፥ ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ንጹሃንን ለመጠበቅና አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው።
ጦርነቱ እንደተጀመረ ለፍልስጤም የ20 ሚሊየን ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግ ያዘዙት ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ “ጋላንት ናይት 3” የሚል መጠሪያ ያለውን ዘመቻ አቋቁመው ወደ ጋዛ ድጋፍ እየተላከ ነው።
ኤምሬትስ በ55 ቀናት ውስጥ ከ9 ሺህ 300 ቶን በላይ ስብአዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ መላኳን በቅርቡ መግለጿ ይታወሳል።
ሀገሪቱ በጋዛ 150 አልጋዎች ያሉት ፊልድ ሆስፒታል በመክፈትም በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ፍልስጤማውያን ቀዶ ጥገናን ጨምሮ የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በጦርነቱ የቆሰሉ 1 ፍልስጤማውያን ህጻናት በሀገሪቱ የመንግስት ሆስፒታሎች ህክምና እንዲያገኙና እንዲጠለሉው መፈቀዷ አይዘነጋም።
ከ24 ሺህ 400 በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት የጋዛን ከግማሽ በላይ የጤና ተቋማት አፈራርሷል።
ከ21 በላይ ሆስፒታሎች ስራ ማቆማቸውን ተከትሎም በህክምና እጦት በርካታ ሰዎች ህይወታቸው እያለፈ መሆኑን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።